የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለ“የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማህበር የመቶ ሺህ ብር ድጋፍ አደረገ፡፡
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለ“የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማህበር የመቶ ሺህ ብር ድጋፍ አደረገ፡፡
ሚኒስቴሩ ለየወደቁት አንሱ የነዳያን መርጃ ማህበር ድጋፍ ያደረገዉ የመጭዉን የፋሲካ በዓል ምክንያት በማድረግ ነዉ፡፡
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታሁን አብዲሳ እንደተናገሩት፣ በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ ወገኖችን መንግስታዊና ህዝባዊ አቅምን በማቀናጀት ችግራቸውን ልናቃልል ይገባል ብለዋል፡፡
በዚህ ረገድ “የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማኅበር” ላለፉት ሃያ ዓመታት የተወጣውንና እየተወጣ ያለውን ኃላፊነት ሚኒስትር ዴኤታው አድንቀው፣ በተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የተነሳ ለጉዳት የተዳረጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ከገቡበት ችግር ወጥተው ለመደበኛ አኗኗር እንዲበቁና የልማት ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ የሁሉም ሀላፊነት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የማህበሩ የቦርድ ሊቀንበር አቶ አራጋው ሀይሌ በበኩላቸው ማህበሩ ከተመሰረተ ጀምሮ 1ሺህ 285 ሰዎችን በምግብ፣ በመጠለያና በህክምና መርዳት መቻሉን ተናግረው፤ የችግሩን ግዝፈት ከግንዛቤ በማስገባት ማህበሩ በተቋሙ ውስጥ ከሚያደርገው ድጋፍ ባለፈ ቤት ለቤት የመሰረታዊ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
ማህበሩ ከአዲስ አበባ አስተዳደር በተሰጠው ቦታ የአረጋውያን መጠለያ፣ የአስተዳደር ቢሮ፣ ክሊኒክ እና አጋዥ ክፍሎችን የያዘ የመጦርያ ማእከል ተገንብቶ ከ2008 ዓ.ም ስራ መጀመሩን አንስተው የህክምና መስጫው የግብዓት እና የሰው ኃይል እጥረት ያለበት በመሆኑ የመንግስት ተቋማት እና የተለያዩ ሲቪል ማህበራት እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማህበር በ1991 ዓ.ም ሁለት በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር መቋቋሙ የሚታወስ ነው፡፡