የመሪያቸው ሸንቃጣነት ያሳሰባቸው ሰሜን ኮሪያዊያን…
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 22፣ 2013 ሰሜን ኮሪያዊያን የመሪያቸውን ክብደት መቀነስ ከጤናቸው ሁኔታ ጋር አያይዘው ሀሳብ ገብቷቸዋል ተባለ፡፡ ለወትሮው በሰፋፊ ልብሶቻቸው ፈርጠም ባለ ሰውነታቸው የሚታወቁት ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሸንቀጥ ብለው ታይተዋል ነው የተባለው፡፡ ይህ ደግሞ ለሰሜን ኮሪያዊያን እንደ መልካም ዜና እንደማይቆጠር መገናኛ ብዙሃን በስፋት እየዘገቡት ይገኛሉ፡፡
የሀገሪቱ ቴሌቭዥን ጣቢያ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ይዞት በወጣው ዜና ህዝቡ የቀጨጨውን የመሪውን ምስል ባየ ጊዜ ልቡ በሀዘን ተነክቷል ማለቱን አልጀዚራ በዘገባው አስነብቧል፡፡ የቀድሞውን ሰውነታቸውን ከአሁኑ ጋር በማነፃፀር ኪም ከ10 አስከ 20 ኪሎ ክብደት ሳይቀንሱ እንዳልቀሩ አስተያየታቸውን የሚሰጡ አልጠፉም፡፡
ይሁን እንጂ የቅርብ ጓዶቻቸው ሀገሪቱ የገባችበት የጤና ቀውስና የምግብ እጥረት በእጅጉ ስላስጨነቃቸው ይህን ለመቀልበስ ራሳቸውን በከባድ ስራ ስለተጠመዱ ነው በማለት ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ያላቸውን ታማኝነት ለማሳየት ሲሞክሩ ታይተዋል ይላል ዘገባው አክሎ፡፡ ኪም ጆንግ ኡን እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2014 ከአንድ ወር በላይ ከህዝብ እይታ ጠፍተው በመክረማቸው የጤናቸው ሁኔታ ተዛብቷል አልያም ሞተዋል የሚል ወሬ ሲናፈስ መቆየቱ ይታወሳል፡፡