ዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ መርሃ ግብር በቀጣይ ዓመት ሊጀመር ነው
የከተሞች የምግብ ዋስትና አካል የሆነው ዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ መርሃ ግብር በቀጣይ ዓመት ሊጀመር መሆኑን የፌዴራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ ።
ኤጀንሲው እንዳስታወቀው ወደ መርሀ ግብሩ የሚገቡት ሰዎች በምግብ ዋስትና ተጠቃሚ በመሆን ላይ የሚገኙ ናቸው።
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን አሰፋ እንዳሉት መርሀ ግብሩ ዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙት የህብረተሰብ ክፍሎች ኑሯቸውን ከመደጎም አልፈው ራሳቸውን የሚችሉበት ነው ።
የዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ መርሀግብሩን ወደ ስራ ለማስገባት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ነው አቶ ሰሎሞን የተናገሩት።
ለዚህም ከወዲሁ ተጠቃሚዎቹ ወደ ፊት ሊሰማሩባቸው የሚችሉባቸውን የስራ እቅዶች በማዘጋጀት ሊሰማሩበት ባቀዱት ስራ ላይም ስልጠናዎችን እየወሰዱ ነው ብለዋል።
እስካሁን 51 ሺ ሰዎች ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ የስራ እቅዳቸውን ማቅረባቸው የተገለጸ ሲሆን በቀጣይ ዓመት መርሀ ግብሩ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ኤጀንሲው አስታውቋል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል።