loading
ኮትዲቯሪያዊው ያያ ቱሬ በመጨረሻ ወደ አቴንስ አቅንቷል፡፡

የ35 አመቱ ኮትዲቯሪያዊ አጥቂ ያያ ቱሬ ከማንችስተር ሲቲ የስምንት አመት ቆይታ በኋላ ክለብ አልባ ተጫዋች ሁኖ ነበር፡፡ ተጫዋቹ ከለንደን የእንግሊዝ ክለቦች ጋር ስሙ በሰፊው የተያያዘ ቢሆንም ከአንዱም ክለብ ጋር ስምምነት ሳይፈፅም ወደ አቴንስ በመመለስ ከኦሎምፒያኮስ ጋር ተፈራርሟል፡፡
ያያ ከግሪኩ ክለብ ኦሎምፒያኮስ ጋር ከ12 ዓመት በፊት በ2006 ሁለት የሀገር ውስጥ ዋንጫዎችን በማንሳት ነበር ክለቡን ተሰናብቶ ወደ ፈረንሳይ ማቅናት የቻለው፤ ከዚያም በሞናኮ የአንድ የውድድር አመት ቆይታ ካደረገ በኋላ በ2007 በ10 ሚሊየን ዩሮ ዋጋ ወደ ስፔኑ ክለብ ባርሴሎና አቅንቶ ሶስት ስኬታማ ጊዜን አሳልፏል፡፡
በመቀጠል ከባርሳ ወደ እንግሊዙ ማንችስተር ሲቲ በ2010 ክረምት ወደ 24 ሚሊየን ፓውንድ አካባቢ በሆነ ዋጋ ያቀና ሲሆን ከሲቲ ጋር ያለፉትን ሰምንት አመታት ማሳለፍ ችሏል፡፡
አሁን ደግሞ በ35 አመቱ ወደ ቀድሞ ክለቡ ኦሎምፒያኮስ በማቅናት ስምምነት ፈፅሟል፤ የዝውውሩ ዝርዝር መረጃ ግን እስካሁን በይፋ ባይገለፅም ከስምምነቱ በኋላ በክለቡ ተቀዳሚ ማሊያ ታይቷል፤ ከክለቡ ባለቤት ኢቫንጄሎስ ማሪናኪስ ጋር ተገናኝቷል ተብሏል፡፡
ትላንት ኦሎምፒያኮስ ፓስ ጊያኒናን 5 ለ 0 በረታበት ጨዋታ በክለቡ ደጋፊዎች ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡
ያያ ቱሬ ከስምምነቱ በኋላ ‹‹እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስኩት ከዚህ አስገራሚ ክለብ ጋር ልዩ ትስስር ስላለኝ ነው›› ብሏል፡፡
‹‹በድጋሜ ወደ ክለቡ ስመለስም በኩራት ነው፤ በ2006 ክለቡን ስለቅ እንደምመለስ ቃል ገብቼ ስለነበር ቃሌን መጠበቅ ይኖርብኛል፡፡ ከአውሮፓ፤ ኤሲያ እና አሜሪካ የተለያዩ ክለቦች ጥያቄ ቀርቦልኝ ነበር›› ሲል ጨምሮ ገልጧል፡፡
ያያ ለድል እንደተራበ እና ክለቡን ባለው አቅም በማገዝ በስኬት እንዲጓዝ ለማድረግ እንደተነሳሳ ገልጧል፡፡

አርትስ ስፖርት 28/12/2010

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *