ከ1997 ጀምሮ ታጥረው የቆዩ 154 ቦታዎች ውላቸው ተቋርጦ ለህዝብ ጥቅም ተመላሽ እንዲሆኑ ተወሰነ
አርትስ 12/01/2011
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለረጅም ግዜ ታጥረው የተቀመጡ በመንግስት፣ በግል ባለሀብቶችና በተለያዩ የዲፕሎማቲክ ተቋማት ተይዘው የነበሩ አጠቃላይ ስፋታቸው 4,126,423.83/ አራት ሚሊየን አንድ መቶ ሀያ ስድስት ሺህ አራት መቶ ሀያ አራት ካሬ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ መሬቶች የሊዝ ውላቸው ተቁዋርጦ ተመላሽ እንዲሆኑ ውሳኔ ተላለፈ።
የ አዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ዛሬ ከካቢኔ አባላት ጋር ባደረጉት ስብሰባ ነው ውሳኔውን ያስተላለፉት።
በዚህም መሰረት በፌዴራል መንግስት የተያዙ 11 ቦታዎችን። ጨምሮ በድምሩ 154 በተለያዩ የከተማዋ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ቦታዎች ለህዝብ ጥቅም ተመላሽ ይደረጋሉ።
ቦታዎቹ በዝርዝርም:-
1, ከግል ባለሀብቶች 95 ቦታዎችን በካሬ 456,428.00/ አራት መቶ ሀምሳ ስድስት ሺህ አራት መቶ ሀያ ስምንት ካሬ/
2, ከመንግስት መስሪያ ቤቶች 19 ቦታዎችን በካሬ 127,140.93/ አንድ መቶ ሀያ ሰባት ሺህ አንድ መቶ አርባ አንድ ካሬ/
3, የሸራተን ማስፋፊያን ጨምሮ ከሚድሮክ ግሩፕ 11 ቦታዎችን በካሬ 549,241.00 /አምስት መቶ አርባ ዘጠኝ ሺህ ሁለት መቶ አርባ አንድ ካሬ/
4, ከዲፕሎማቲክ ተቁዋማት 18 ቦታዎችን በካሬ 250,413.89 / ሁለት መቶ ሀምሳ ሺህ አራት መቶ አስራ አራት ካሬ/
5, ከፌደራል ተቁዋማት መከላከያና ቴሌኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬሽንን ጨምሮ 11 ቦታዎችን በካሬ 2,743,200.00 / ሁለት ሚሊየን ሰባት መቶ አርባ ሶስት ሺህ ሁለት መቶ ካሬ
ባጠቃላይ 154 ቦታዎች በካሬ 4,126,423.83/ አራት ሚሊየን አንድ መቶ ሀያ ስድስት ሺህ አራት መቶ ሀያ አራት ካሬ የሊዝ ውላቸው ተቋርጦ ተመላሽ እንዲሆኑ ተወስኗል።
ቦታዎቹ ከ 1997 እስከ 2004 በተለዬዩ ጊዜያት የተላለፉና እስካሁን ምንም አይነት ልማት ሳይከናወንባቸው ታጥረው የተቀመጡ ናቸው።
የከንቲባ ጽ/ቤት እንዳስታወቀው ኢንጅነር ታከለ ኡማ እነዚህና መሰል ቦታዎች የከተማዋን ልማት እንዲጓተት ምክንያት እንደሆኑ ጠቅሰው ይህ ስራ የአንድ ጊዜ ዘመቻ ሳይሆን ከዚ በኋላ አስተዳደሩ ቦታ ወስደው ወደልማት የማይገቡ ማንኛውም የመንግስትም ሆነ የግል ባለሀብት ላይ ጥብቅ ክትትል አድርጎ እርምጃ እንደሚወስድ አሳስበዋል።