ከ12 ከተሞች ተገልጋዮች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በሚሰጠው አገልግሎት አልረካንም አሉ፡፡
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ከዋልታ ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት ጋር በመተባበር በከተሞች የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይይቱ ላይ ከተሞች የመልካም አስተዳደር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ቅንጅታዊ አሰራር ሊከተሉ ይገባል ተብሏል፡፡
ከተሞቻችን የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር እጦት የሰፈነባቸው የምሬት ማዕከል ሆነዋል ያሉት የከተማ ልማትና ቤቶች ሚንስትር አቶ ጃንጥራር አባይ፤ በአመራሮችና ፈጻሚዎች ድክመት፣ የብቃት ችግር ፣ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት አለማቅረብ ለችግሩ መነሻ ሆነዋል ብለዋል፡፡
ችግሩ በስፋት ይስተዋልባቸዋል ከተባሉት መካከል የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ፣ የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ፣የይዞታ አስተዳደር እና የግንባታ ፍቃድ አሰጣጥ ይገኙበታል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ በተመረጡ 12 ከተሞች የተገልጋዮች አስተያየትን መሰረት ያደረገ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡
በጥናት ውጤቱ መሰረት ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ተገልጋዮች የሚሰጠው አገልግሎት እንዳላረካቸው ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ከተሞች መልካም አስተዳደር የሰፈነባቸው ግልጽና ቀልጠፋ አገልግሎቶች እንዲሰጡ ለማድረግ ዘመናዊና የተቀናጀ አሰራር ይዘረጋል ተብሏል፡፡