ከአሜሪካ ጋር ያጋጠመንን ጉዳይ በወዳጆቻችን በኩል ለመፍታት እየሰራን ነው ሲሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ::
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 25፣ 2013 ከአሜሪካ ጋር ያጋጠመንን ጉዳይ በወዳጆቻችን በኩል ለመፍታት እየሰራን ነው ሲሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ:: የኢትዮጵያ መንግስት አሜሪካ አቋሟን ትቀይራለች ብሎ እንደሚያምንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ ገልጸዋል:: የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት ጋዜያዊ መግለጫ የተለያዩ ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን ፣ ከአሜሪካ ጋር የተፈጠረው አለመግባባት የመግለጫቸው ዋነኛ አጀንዳ ነበር፡፡ አሜሪካ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የጣለችውን እገዳ በማስመልከት የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ሀሳባቸውን ማንጸባረቃቸው ይታወቃል፡፡ በተለይም የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በአሜሪካ እገዳ ምክንያት “የነቀዘ ስንዴ ነው የሚቀርብን” ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ይህን በተመለከተ በዛሬው መግለጫቸው አስተያየት የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና “ግለሰቦች የመናገር መብት አላቸው ፤ ይህም የግል አስተያየትና ስሜታቸው ነው” ብለዋል፡፡ የአቶ ሽመልስ “የነቀዘ ስንዴ” ንግግርም የመንግስት አቋም ሳይሆን የግላቸው አስተያየት መሆኑን ነው አምባሳደር ዲና የገለጹት፡፡ በውጭ ጉዳይ ደረጃ “ጉዳዩን የማጋጋል ፍላጎት የለንም” ያሉት ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና “የተፈጠረው ጉዳይ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ በጋራ ወዳጆቻችን በኩል እየተነጋገርን ነው ያለነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የሴናተር ጂም ኢንሆፌ ጉብኝትም የዚሁ አካል ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው ፣ “የአሜሪካ አቋም ይቀየራል ብለን ነው የምናምነው ፣ መቼና እንዴት የሚለው ግን እነሱን የሚመለከት ነው” ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
አምባሳደር ዲና ፣ ሴናተሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዲሁም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር መገናኘታቸውን እና “ውጤታማ ጉብኝት” ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡ ሴናተር ጂም ኢንሆፌ “ለኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ አጋርነታቸውን ያንፀባረቁ ወዳጅ ናቸው” ሲሉም አምባሳደር ዲና ሴናተሩን አድንቀዋል፡፡ አክለውም “የሃገራቱን ግንኙነት ለመታደግ የመንግስትን ጥረት ከነጉድለቱም መደገፍና መነጋገር እንጂ ሌላ ጫና አያስፈለግም የሚሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰው ናቸው” ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪከ ልዩ መልዕክተኛው ጄፍሪ ፌልትማንም ወደ ኢትዮጵያ ዳግም እንደሚመጡ ገልጸው ነገር ግን የሚመጡበት ቀን እንዳልተቆረጠ ነው አምባሳደር ዲና የተናገሩት፡፡ አምባሳደር ዲና “ኢትዮጵያ ካልተገደደች በስተቀር ይኼኛው ይሻለኛል ብላ ፣ የወዳጅ ምርጫ ውስጥ የሚያስገባን ነገር የለም” ያሉም ሲሆን “የውጭ ግንኙነት ፖሊሲውም ይኼን ነው የሚለው ወደ ሰፈር ምርጫ አንሄድም ሲሉ” አክለዋል፡፡
ምናልባትም ሁኔታዎች አስገዳጅ ስለነበሩ “በቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ እንደ ሌሎቹ ድሃ ሃገራት አድርገን ሊሆን ይችላል” ያሉት ቃል አቀባዩ “የኛን የልማት ፍላጎት ችግር ላይ እስካልጣለ ድረስ ወደ ወዳጅ ምርጫ አንሄድም” ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡