እንቦጭ ተመግቦ ሰውን የሚመግበው እንጉዳይ…
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2014 እንቦጭን በመመገብ ማጥፋት የሚችል የእንጉዳይ ዝርያ በምርምር መገኘቱን የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ። በኢትዮጵያ ደን ልማት የደን ውጤቶች እና ኢኖቬሽን ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ገበየሁ እንቦጭ አረምን ለማጥፋት ብዙ ጥረትና ምርምር ሲደረግ መቆየቱን ገልጸው በአሁኑ ወቅት እንቦጭን በመመገብ
የሚያጠፋ እንጉዳይ ዝርያ በምርምር ተገኝቷል ብለዋል።
በምርምሩ መሠረት እንቦጭ ያለበት ቦታ ላይ እንጉዳዩ እንዲዘራ ይደረጋል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ እንጉዳዩ ሲበቅል እንቦጭን እንደ ምግብ በመጠቀም የሚያድግ ይሆናል፤ በዚህ ሂደት እንጉዳዩ ለሰው ልጆች ምግብነት የሚውል ሲሆን እንቦጩ ደግሞ እየጠፋ ይሄዳል ብለዋል። ከዚህ ባለፈ ተቋሙ መጤ አረሞችን ወደ ጥቅም ሰጪ ነገር ለመቀየር የተለያዩ ምርምሮች እና የቴክኖሎጂ አማራጮች ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በተለምዶ የወያኔ ተክል ተብሎ የሚጠራው የዛፍ ዝርያ በአፋርና ሱማሌ ክልሎች አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ተንሰራፍቷል ብለዋል አቶ ዳንኤል፡፡ የዚህን ዛፍ ስርጭት ሙሉ ለሙሉ መግታት ወይንም ደግሞ ስርጭቱን በሂደት ማቆም እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ይህ የዛፍ ዝርያ በአርብቶ አደርነት በሚተዳደረው የአፋር እና ሱማሌ ክልል ማኅበረሰብ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየፈጠረ ሲሆን፣ በወተት እና ሥጋ ምርት ላይም አሉታዊ ጫና አሳድሯል ነው ያሉት። በእነዚህ አካባቢዎች የሳር ግጦሽ ወሳኝ ሲሆን ይህ አረም ግን ሳር፣ ቅጠላ ቅጠልና ሌሎች የዕፅዋት ዝርያዎች እንዲጠፉ እያደረገ ነው ማለታቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅተ ዘግቧል። ከዚህም በተጨማሪ የከርሰ ምድር ውኃን በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚመጥና ከፍተኛ ትነት በመኖሩ የሥነ- ምኅዳር መዛባትን እያስከተለ መሆኑንም አስረድተዋል።