እስካሁን የምርጫ ውጤት ተጠቃልሎ አልደረሰኝም-ምርጫ ቦርድ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 25፣ 2013 በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን የሁሉንም ምርጫ ክልሎች ውጤት ይፋ ማድረግ አለመቻሉን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ። እስካሁን ባለው ሂደት ምርጫ ከተካሄደባቸው የምርጫ ክልሎች የ26ቱ ውጤት አለመድረሱን ቦርዱ አስታውቋል። የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ፤ በድምር መዘግየት፣ በትራንስፖርት ችግር እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች አቤቱታ ምክንያት የምርጫ ክልሎች ውጤት ወደ ማዕከል ተጠቃሎ አልደረሰም ብለዋል። በጋምቤላ 2፣ በአፋር 7፣ በአዲስ አበባ 8፣ በኦሮሚያ 4፣ በአማራ 3፣ በደቡብ ክልል 2 የምርጫ ክልሎች ውጤቶች አለመድረሳቸውን ጠቅሰዋል።
ለቦርዱ ውጤት አያድርሱ እንጂ የምርጫ ክልሎቹ በየአካባቢያቸው የምርጫ ውጤት የተለጠፈ መሆኑን ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል ነገሌ ምርጫ ክልል አንድ የግል ተወዳዳሪ በምርጫ ወረቀቱ ላይ ስሜ አልተካተተም በሚል ያቀረቡት ቅሬታ ተቀባይነት በማግኘቱ ቦርዱ ቅሬታው አሳማኝ መሆኑን አረጋግጦ ምርጫ እንዳይካሄድ ወስኖ እንደነበርም አንስተዋል። የአካባቢ ማህበረሰብ ምርጫው መሰረዙን ባለመስማቱ በምርጫ ክልሉ ካሉት 139 ምርጫ ጣቢያዎች በ105ቱ ምርጫ መካሄዱ በመረጋገጡ ድምጹ እንዳይቆጠር የድምጽ መስጫ ወረቀቱ ታሽጎ እንዲቀመጥ ተደርጎ እንደነበር አስታውሰዋል። ሆኖም ቅሬታ አቅራቢው የግል ተወዳዳሪ ምርጫ ከተደረገ በኋላ በእኔ ምክንያት ድጋሜ ምርጫ መካሄድ የለበትም በማለቱ ውጤቱ እንዲቆጠር ቦርዱ መወሰኑንም ገልጸዋል።