ኢንተር ሚላን ከኮፓ ኢጣሊያ ውድድር ውጭ ሁኗል
ኢንተር ሚላን ከኮፓ ኢጣሊያ ውድድር ውጭ ሁኗል
የኮፓ ኢጣሊያ የሩብ ፍፃሜ አንድ ጨዋታ ትናንት ምሽት ተከናውኗል፡፡
ጨዋታው በኢንተር ሚላን እና ላትሲዮ መካከል ጁሴፔ ሜዛ ላይ የተከናወነ ሲሆን ሙሉ ጨዋታው ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቅቋል፤ ከዚያም በተሰጠው ተጨማሪ 30 ደቂቃ ሁለቱ ቡድኖች ግቦችን በማስቆጠር በአንድ አቻ ውጤት ሳይሸናነፉ አሁንም ተለያይተዋል፡፡
ቺሮ ኢሞቢሌ በ108ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥሮ የሮማውን ቡድን ቀዳሚ ቢያደርግም የ30 ደቂቃው ጭማሪ አልቆ፤ በተሰጠው የባከነ ሰዓት ጭማሪ የኢንተሩ አምበል ማውሮ ኢካርዲ በፍፁም ቅጣት ምት አቻ አድርጓል፡፡
በተሰጠው የመለያ ፍፁም ቅጣት ምት እንግዳው ላትሲዮ 4 ለ 3 በመርታት ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል፡፡
የላትሲዮው ሪዛ ዱርሚዚ የለጋት የፍፁም ቅጣት ምት፤ በኢንተሩ ግብ ጠባቂ ሳሚር ሀንዳኖቪች ግብ ከመሆን ብትድንም፤ ቺሮ ኢሞቢሌ፣ ማርኮ ፓሮሎ፣ ፍራንችዞ አቼርቢ እና ሉካስ ሌቫ አስቆጥረዋል፡፡
የላትሲዮው ግብ ጠባቂ ቶማስ ስትራኮሻ፤ የኢንተሮቹን ላውታሮ ማርቲኔዝ እና ራጃ ናይንጎላን ምቶች አምክኗል፡፡
የግማሽ ፍፃሜው ዙር በደርሶ መልስ የሚከናወን ሲሆን የካቲት 27 እና ሚያዚያ 24/2019 ይደረጋሉ፡፡ በደርሶ መልስ የሚጫወቱት ቡድኖች ላትሲዮ ከ ኤስ ሚላን እንዲሁም አታላንታ ከፊዮረንቲና ይፋለማሉ፡፡
የፍፃሜው ጨዋታ በስታዲዮ ኦሎምፒኮ ሮም ላይ ግንቦት 15 ይደረጋል ተብሏል፡፡