ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ፊታውራሪ ነች ተባለ፡፡
አርትስ 30/12/2010
ዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት (Global Green Growth Institute-GGGI) የተሰኘ ዓለም ዓቀፍ የበየነ መንግስታት ተቋም በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅህፈትቤት ለመክፈት የሚያስችለው ስምምነት ፈረመ፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እና የተቋሙ የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ ስራ አስኪያጅ ዴክሲፖስ አጉሪደስ ናቸው ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት በድረገፁ እንዳስነበበው ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ፣ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ቀርፃ ስራ ላይ በማዋል ተጨባጭ ውጤት በማስመዝገብ ዘላቂ ልማትና የአረንጓዴ ልማት የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ለዓለም ማሳየቷን የጽህፈትቤቱ መከፈት ምስክር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተቋሙ የአፍሪካ ቅርንጫፍ ጽህፈትቤት መሆኗ ሀገሪቱ በአፍሪካ ደረጃ እንዲሁም በዓለምአቀፍ መድረኮች ለአረንጓዴ ልማት የነበራትን የመሪነት ሚና እንደሚያጎላውም ተናግረዋል፡፡
ዴክሲፖስ አጉሪደስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የተቋሙ የአፍሪካ ጽህፈትቤት እንድታስተናግድ የተመረጠችው በአፍሪካ ብሎም በዓለምአቀፍ ደረጃ የአረንጓዴ ልማት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳ ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆኗ ነው ብለዋል፡፡
ቅርንጫፍ ጽህፈትቤቱ ሀገሪቱ የጀመረችውን ዘላቂ ልማት በመደገፍ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡