ኢትዮጵያ እና ሱዳን በድንበር ማካለል ዙሪያ ጎንደር ውስጥ ውይይት ሊያደርጉ ነው
አርትስ 21/02/2011
ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር ማካለል ዙሪያ በመጪው ህዳር ጎንደር ከተማ ላይ ውይይት ሊያካሂዱ መሆኑ ተነግሯል ።
ሱዳን ትሪቢዩን ገዳሪፍ የምትባለውን የሱዳን ግዛት አስተዳዳሪ ኦስማን መሃመድ አህመድን ጠቅሶ እንደዘገበው ውይይቱ በመጪው የፈረንጆቹ ኖቬምበር መጀመሪያ የሚካሄድ ሲሆን ከኢትዮጵያ ጋር የሚዋሰኑ የሱዳን ግዛት ሀላፊዎች በሙሉ ይገኛሉ ብለዋል።
ውይይቱ ላይ አልጋልባት፣ አልሸሪቅ፣አል ቁረሻ እና ባሱንዳ የሚባሉት ከኢትዮጲያ ጋር በድንበር የሚዋሰኑ የሱዳን ግዛቶች አስተዳዳሪዎች እንደሚገኙ ተነግሯል። አስተዳዳሪዎቹ ከኢትዮጲያ መንግስት ጋር በድንበር ማካለል፣ በህገ ወጥ የሰዎች እና የጦር መሳሪያዎች ዝውውር እና በድንበር አካባቢበሚገኙ ታጣቂዎች ዙሪያ ይወያያሉም ተብሏል።
እንደ አስተዳዳሪው ገለፃ ኢትዮጲያ እና ካርቱምን በሚያገናኟቸው የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይም ውይይት የሚደረግ ሲሆን የሁለቱ ሃገራት የድንበር ጉዳይ አወዛጋቢ እንዲሁም በህገወጥ ስደት እና መሳሪያ ዝውውር ምክንያት ስጋት ሆኖ የቆየ ነው ብለዋል። በጎንደር የሚካሄደው ውይይትም ይህንኑ ያማከለ ነው ብለዋል፡፡
እንደሱዳን ትሪቢዩን ገለጻ የአልፋሺቃ እና የገዳሪፍ የሱዳን ግዛቶች አርሶአደሮች በድንበር አካባቢ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አርሶአደሮች ጋር ያላቸውን አለመስማማትም በውይይታቸው እንደሚያነሱ ነው የገለጹት ።