ኢትዮጵያ ለስደተኞች የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል የውጪጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ
አርትስ 15/01/2011
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው 73ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ለሚመጡ ስደተኞች የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልፀዋል ፡፡
ለዚህም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብራ እንደምትሰራ ገልፀው ሀገራትና የአለምአቀፉ ማህበረሰብ የስደተኞችን መነሻ ችግር ለመፍታት ጥረት ማድረግ አለባቸውም ብለዋል ፡፡
የአለምአቀፉ ማህበረሰብ ስደተኞችን የሚያስጠልሉ ሀገራት የሚደርስባቸውን ጫና መጋራት እንዳለበትም እና ስደተኛ ተቀባይ ሀገራትም የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል ፡፡የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፊሊፕ ግራንዴ በበኩላቸው አለምአቀፉ ማህበረሰብ ስደተኞችን የመቀበልና የመደገፍ ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል ፡፡
ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ፣ ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ታባንግ ዴንግ ጋይ እንዲሁም ከሩዋንዳ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦሊቨር ኑሃንገሬህ ጋር የአገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የበለጠ በሚጎለብቱባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተነጋግረዋል።