ኢሶህዴፓ ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል አደረጃጀቴን እያጠናከርኩ ነው አለ
ኢሶህዴፓ ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል አደረጃጀቴን እያጠናከርኩ ነው አለ
የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ / ኢሶህዴፓ/ የለውጥ ሂደቱን ለማስቀጠል በሚያስችለኝ ቁመና ላይ ለመገኘት የውስጥ አደረጃጀቴን ማጠናከር ጀምሬያለሁ አለ።
ለመካከለኛው አመራሮች በተዘጋጀው የሃገራዊ ለውጥ ግንዛቤ መድረክ በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።
መድረኩን የመሩት የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ አህመድ ሽዴ መሀመድ እንዳሉት ፓርቲው በክልሉ ተከስቶ በነበረው ቀውስ ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት የመሩና የተሳተፉ አመራር አባላቱን በማስወገድ በአዲስ አመራር ተክቷል።
ከሁሉም በላይ በሀገሪቱ የተጀመረው ለውጥ እንዲጠናከር ለማድረግ የክልሉን መንግስት የሚመራው ኢሶህዴፓ ለከፍተኛና መካከለኛ አመራሩ እንዲሁም ለአባላቱ ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሃገራዊ ለውጡ ትሩፋቶች መካከል የትጥቅ ትግል ሲያካሄዱ የነበሩ ፓርቲዎች ሰላማዊ ትግል ውስጥ እንዲገቡ መደረጉ ለሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በውጪ የሚገኝ ተቃዋሚ ኃይል የሌለበት ወቅት ላይ ደርሰናል ያሉት አቶ አህመድ የለውጥ አመራሩ ከጎረቤት ሀገራትም የጋራ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲኖር ውጤታማ ስራ ማከናወኑን አስረድተዋል፡፡
አቶ አህመድ እንዳሉት ሀገራዊ የለውጥ አመራሩና ኢሶህዴፓ ከኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር ጋር የደረሰው የሰላም ስምምነት ሌላው ማሳያ ነው።
ኢዜአ እንደዘገበው ከአንድ ሺህ ስድስት መቶ በላይ የኢሶህዴፓ መካከለኛ አመራር አባላት እስከነገ በሚቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እየተሳተፉ ነው፡፡