አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ መመረጥ ደስታቸውን ገለጹ
አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ መመረጥ ደስታቸውን ገለጹ
የኢሲኤ ዋና ጸሃፊና የኬንያ ፕሬዚዳንትም ተመሳሳይ የደስታ መግለጫ ልከዋል
16/02/2011
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ለፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የደስታ መግለጫ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሃፊ ዶክተር ቬራ ሶንግዌ እና የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታም ተመሳሳይ መልዕክት ልከዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የእንኳን ደስ አለዎት መልእክቱን ያስተላለፉት በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ነው ።
ዋና ጸሃፊው ለመላው ኢትዮጵያውያን ባስተላለፉት መልእክት፥ የመጀመሪያዋን ሴት ፕሬዚዳንት በመምረጣችሁ እና አዲስ በተዋቀረው ካቢኔ ውስጥ ሴቶች ከፍተኛ ሀላፊነት እንዲይዙ በማድረጋችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
አፍሪካ ሴቶችን ወደ ከፍተኛ ሀላፊነት በማምጣት ለሌሎች አርአያ በሚሆን መልኩ ቅድሚያ በመውሰድ እየሰራች ነው ያሉት ዋና ፀሃፊው፤ የሴቶች አመራር ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ መሆኑንም እያረጋገጡ መሆኑንም ገልፀዋል።
በተመሳሳይ መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ቬራ ሶንግዌ በትዊተር ገፃቸዉ “የረጅም ዓመታት የዲፕሎማሲ ልምድ ባለቤት የሆኑት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በታታሪነትዎ ላገኙት ከፍተኛ ኃላፊነት እንኳን ደስ አለዎት” ብለዋቸዋል ፡፡
የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታም ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የደስታ መግለጫ የላኩ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን ሴት ፕሬዚዳንት መምረጧ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ለአፍሪካ ብሎም ለመላው ዓለም ታሪካዊ ክስተት ነው ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለዉም “የሳህለወርቅ ዘውዴ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጥ የአይበገሬዎቹ የአፍሪካ ሴቶች ዕጣ ፈንታ እየተቀየረ ለመሆኑ ማሳያ ነው” ብለዋል::