loading
አቶ ገዱ የዓለም ምግብ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 19 ፣ 2012

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የዓለም ምግብ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑትን ዴቪድ ቢስሊይን ዛሬ በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሁለቱ  ወገኖች የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት፣ የበረሃ አንበጣ እና የጎርፍ አደጋ በቀጠናው ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።በተጨማሪም የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ መረጃ ተለዋውጠዋል።አቶ ገዱ የዓለም ምግብ ድርጅት ለኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀው፤ ኢትዮጵያ ከድርጅቱ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።

በኮሮናቫይረስ  ምክንያት በዓለም ላይ እየደረሰ ባለው የሰው ሞት የተማቸውን ሃዘንም ገልጸዋል።በኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ ያለበትን ደረጃ እና ኢትዮጵያ ወረርሽኙን ለመግታት እያከናወነች ያለውን ስራ በተመለከተም ገለጻ አድርገዋል።

የበረሃ  አንበጣና የጎርፍ አደጋ በኢትዮጵያ እና በጎረቤት አገራት እያደረሰ ያለውን ጉዳት በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል።የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ከምንጊዜውም በላይ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ድጋፍ በእጅጉ እንደሚፈልግና የዓለም የምግብ ድርጅት እያደረገ ያለውን ድጋፍ በተሻለ አጠናከሮ እንዲቀጥል አቶ ገዱ ጥሪ አቅርበዋል።አቶ ገዱ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንበታ የደረሰበትን ደረጃና በአትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል ሲደረጉ የቆዩ ውይይቶችን በተመለከተም ገለጻ አድርገዋል።ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሶስቱ አገራት ያላቸውን ልዩነት በውይይትና በድርድር እንዲፈቱ ድጋፍ እንዲያደርግም አቶ ገዱ ጠይቀዋል።

የዓለም  ምግብ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዴቪድ ቢስሊይን በበኩላቸው ድርጅታቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።ኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስን፣ የበረሃ አንበጣንና የጎርፍ አደጋን ለመከላከል እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴም አድንቀዋል።የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የዓለም ስጋት በመሆኑ የሁሉም አካላት ትብብር ወሳኝ መሆኑን ዴቪድ ቢስሊይን ገልጸዋል።ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ሶስቱ አገራት ልዩነታቸውን በውይይት መፍታት አለባቸው ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋ ሲል የውጭ ገዳይ  ቃለ አቀባይ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

 

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *