loading
ቻይና ለ50 ዓመታት የዘለቀውን አጋርነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች::

አዲስ አበባ፣ጥር 28፣ 2013 ቻይና ለ50 ዓመታት የዘለቀውን አጋርነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች:: የኢፌድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩአንን ተቀብለው ያነጋገሩ ሲሆኑ : በሁለቱ አገሮች መካከል ስላለው የተጠናከረ ግንኙነትና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል። አምባሳደር ዣኦ ዢዩአን ኢትዮጵያና ቻይና 50 አመታትን የዘለቀ በመተባባር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ወዳጅነት እንዳላቸው አንስተዋል፡፡

በዚህም በሁለቱ አገሮች መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ዲፕሎማሲ ግንኙነት መፈጠሩን ገልጸዋል። በፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትም እጅግ ውጤታማ ስራዎች መመዝገባቸውንም ተናግረው፤ በተለይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም በተከሰተበት ወቅት በአገሮች መካከል የነበረው የእርስ በርስ መረዳዳት ተጠቃሽ እንደነበር ነው የጠቀሱት፡፡ ቻይና በኢትዮጵያ በርካታ ፕሮጀክቶችን መገንባቷን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዲያድግ ቻይና 50 ሺህ ዜጎቿን በተለያዩ የስራ መስኮች አሰማርታ የአቅማቸው ድርሻ በመወጣት ላይ ይገኛሉ” ብለዋል፡፡

በዚህም ለአንድ ሚሊየን ኢትዮጵያውያን የስራ ዕድል መፈጠሩንም ነው ያስረዱት፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው ቻይናና ኢትዮጵያ የቆየ ወዳጅነት የተጠናከረ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በኢኮኖሚው ረገድ ኢትዮጵያ ከቻይና ትልቅ ትምህርት እንደምታገኝምገልጸዋል፡፡ አያይዘውም በቅርቡ በትግራይ ክልል የተከሰተው ግጭት የውስጥ ጉዳይና ህግ የማስከበር ተግባር መሆኑን ጠቁመው፤ አሁን ላይ አገሪቱ የተረጋጋ ሁኔታ ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡

በቀጣይም የቻይና መንግሥት በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ያለው ወሳኝ ሚና የሚቀጥልና የበለጠ የሚጠናከር መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ አምባሳደር ዣኦ ዢዩአን በበኩላቸው ቻይና በሌሎች አገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የማትገባ አገር መሆኗን ገልጸው፤ በትግራይ ክልል የተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ውጤታማ ሆኖ መጠናቀቁን አንስተዋል፡፡ በቀጣይም ኢትዮጵያ ለምታደርገው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ቻይና አጋር መሆኗን በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩአን መግለጻቸውን ምክር ቤቱ ገልጿል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *