ብሩንዲ የፕሬዝዳንቱን ምስል አበላሽታችኋል ብላ ያሰረቻቸውን ልጃገረዶች ፈታች፡፡
ብሩንዲ የፕሬዝዳንቱን ምስል አበላሽታችኋል ብላ ያሰረቻቸውን ልጃገረዶች ፈታች፡፡
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ሶስት የብሩንዲ ተማሪዎች ፕሬዝዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ላይ አላግጣችኋል ተብለው ለእስር ተዳርገው ነበር፡፡
ተማሪዎቹ የፕሬዝዳንቱን ፊት በሰክርቢቶ ሞነጫጭረዋል ተብለው ነው የታሰሩት ተብሏል፡፡
እነዚህ ተማሪዎች ፕሬዝዳንቱን ሰድበዋል በሚል በአቃቤ ህግ በቀረበባቸው ክስ በአንድ የወረዳ ፍርድ ቤት መቅረብ እና እስር ቤት መግባት ግድ ሆኖባቸዋል፡፡
ደይሊ ኔሽን እንደዘገበው ብሩንዲ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና ሲበዛባት እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑትን ተማሪዎች ነው ከእስር የፈታቸው፡፡
በተለይ ልጆቹ እድሜያቸው ዝቅተኛ መሆኑ በዓለም ዙሪያ ያሉ የመብት ተሟጋች ተቋማት እና ግለሰቦችን ጭምር በፍጥነት ከእስር እንዲፈቱ የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ ገፋፍቷቸዋል፡፡
የብሩንዲ ፍትህ ሚንስትር ኤሚ ላውረንቴ ካንያና ግን በሀገራችን ህግ መሰረት አንድ ሰው 15 ዓመት ከሞላው ለሰራው ወንጀል ሙሉ ሀላፊነቱን ይወስዳል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሯ አክለውም ወላጆች ልጆቻቸው ትምህርት ላይ እንዲያተኩሩ እንዲሁም ልጆች ደግሞ በለ ስልጣናትን እንዲያከብሩ በተደጋጋሚ ተነግሯቸዋል ግን ትኩረት ሲሰጡት አይስተዋልም ብለዋል፡፡
ሂውማን ራይትስ ዋች የተባለው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም በበኩሉ በሀገሪቱ ስንት ከባባድ ወንጀሎች እየተፈፀሙ ህፃናትን የሀገር መሪ ምስል አበላሹ ብሎ ማሰር ተቀባይነት እንደሌለው ገልጿል፡፡
መንገሻ ዓለሙ