loading
ባርሴሎና የላሊጋውን መሪነት ያጠናከረበትን ድል አስመዝግቧል

ባርሴሎና የላሊጋውን መሪነት ያጠናከረበትን ድል አስመዝግቧል

የ20ኛው ሳምንት የስፔን ላሊጋ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ተካሂደዋል፡፡

ትናንት በርካታ ጨዋታዎች ሲከናወኑ፤ በሊጉ አናት ላይ የተቀመጠው የካታላኑ ባርሴሎና በኑካምፕ ሌጋኔስን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ረትቷል፡፡

የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ሊዮኔል ሜሲ እና ሊዩስ ሱዋሬዝ እንዲሁም ፈረንሳዊው ኦስማን ዴምቤሌ የግቦቹ ባለቤቶች ናቸው፡፡ በላሊጋው ሜሲ 18 ያህል ግቦችን በተቃራኒ መረብ ላይ በማሳረፍ ሲመራ፤ ሱዋሬዝ በ15 ይከተለዋል፡፡ ማርቲን ብራይትዋይት የእንግዳውን ቡድን ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡

ድሉን ተከትሎ በኤርኔስቶ ቫልቬርዴ የሚሰለጥነው ባርሳ በ20 ጨዋታዎች ላይ 46 ነጥቦችን በመሰብሰብ ሊጉን መምራቱን አጠናክሯል፡፡ ከተከታዮቹ አትሌቲኮ ማድሪድ በ5 ነጥብ፤ ከተቀናቃኙ ሪያል ማድሪድ ደግሞ በ10 ነጥብ በመላቅ ቁልቁል ይመለከታቸዋል፡፡

በሌሎች ግጥሚያዎች ሪያል ቤቲስ 3 ለ 2 ጅሮና፣ ሌቫንቴ  2 ለ 0 ሪያል ቫያዶሊድ ሲረቱ፤ ቪያሪያል 1 ለ 1 አትሌቲኮ ቢልባኦ እንዲሁም ራዮ ቫይካኖ 2 ለ 2 ሪያል ሶሴዳድ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡

ከትናንት በስቲያ ደግሞ ሪያል ማድሪድ በሳንቲያጎ ቤርናባው ሲቪያን በካስሜሮ እና ሞድሪች ጎሎች 2 ለ 0 ሲያሸንፍ፤ አትሌቲኮ ማድሪድ ከሜዳው ውጭ ሁሴካን በኸርናንዴዝ፣ አርያስ እና ኮኬ ግቦች 3 ለ 0 ረትቷል፡፡ ቫሌንሲያ ሴልታ ቪጎን 2 ለ 1 ድል አድርጓል፡፡

ዛሬ ምሽት 5፡00 ኤይባር ከ ኢስፓኞል ይገናኛሉ፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *