loading
በኮፓ አሜሪካ ብራዚል ግማሽ ፍፃሜውን ስትቀላቀል፤ አርጀንቲና ዛሬ ምሽት ተጠባቂ ጨዋታ ይኖራታል፡፡

የውድድሩ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ትናንት ከእኩለ ሌሊት በኋላ መከናወን የጀመሩ ሲሆን ዛሬ ምሽት እና በቀጣዮቹ ቀናት ይደረጋሉ፡፡

የውድደሩ አዘጋጅ ብራዚል አሬና ዶ ግሬሚዮ ላይ ፓራጓይን በ45 ሺ ተመልካቾች ፊት በመለያ ፍፁም ቅጣት ምት አሸንፋ ግማሽ ፍፃሜውን መቀላቀሏን አረጋግጣለች፡፡

በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ግብ ማስቆጠር ባለመቻላቸው ወደ ግማሽ ፍፃሜው የሚያልፈውን ቡድን ለመለየት በተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት ብራዚል 4 ለ 3 አሸንፋለች፡፡

ፋቢያን ባልቡኤና ከፓራጓይ በኩል በቀይ ካርድ ከሜዳ ቢሰናበትም፤ ሴልካኦ ከ30 ደቂቃ በላይ ለሚበልጥ ጊዜ የነበራቸውን የቁጥር ብልጫ መጠቀም አልቻሉም፡፡

በመለያ ፍፁም ቅጣት ምቱ ወቅት ዊሊያን፣ ማርኪንሆስ፣ ፊሊፔ ኮቲንሆ እና ጋብሪል ጄሱስ ለብራዚል ቢያስቆጥሩም ሮቤርቶ ፊርሚኖ አምክኗል፡፡

የኮፓ አሜሪካ ሩብ ፍፃሜ ሁለተኛ ጨዋታ ደግሞ ዛሬ ምሽት ሲቀጥል በምድብ B አራት ነጥቦችን በመያዝ ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው አርጀንቲና ሪዮ ዴ ጄኔሮ በሚገኘው እስታዲዮ ዶ ማራካኛ በምድብ A አምስት ነጥብ በመሰብሰብ ብራዚልን ተከትላ ካጠናቀቀችው ቬንዙዌላ ጋር ብርቱ ፉክክር ታደርጋለች፡፡

በአሰልጣኝ ሊዮኔል ስካሎኒ የምትሰለጥነው አርጀንቲና በሊዮኔል ሜሲ ፊት አውራሪነት እየተመራች ደካማ የውድድር ጊዜ እያሳለፈች ቢሆንም አሁንም ለሻምፒዮንነት ከሚጠበቁ ቡድኖች አንዷ ናት፡፡

በምሽቱ ጨዋታም ቬንዙዌላ ለአልባሴልስቲዎቹ ፈታኝ ልትሆን እንደምትችል ይጠበቃል፡፡

የአርጀንቲና እና ቬንዙዌላ አሸናፊ በግማሽ ፍፃሜው ከብራዚል ይገናኛል፡፡

ሌሊት 8፡00 ሰዓት ላይ ደግሞ በምድብ B ላይ ሶስቱንም የጨዋታ መርኃግብር በድል የተወጣችው ኮሎምቢያ በአሬና ኮሪንታያንስ ከቺሊ ጋር ትጫወታለች፡፡

ቺሊ ከምድብ C ሁለት ጨዋታዎችን በመርታት ስድስት ነጥብ በመያዝ ሁለተኛ ሆና አጠናቅቃለች፤ ከካርሎስ ኪሮዧ ኮሎምቢያ ጋርም ብርቱ ትንቅንቅ ይኖራቸዋል ተብሎ እየተነገረ ይገኛል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *