loading
በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ቀያዮቹ እና ውሃ ሰማያዊዎቹ አሁንም ትንቅንቃቸው ቀጥሏል

የሊጉ የ34ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዓርብ ጀምሮ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ተከናውነዋል፡፡

በትናንትናው ዕለት በሳምንቱ ተጠባቂ በነበረው ፍልሚያ ሊቨርፑል መርሲ ሳይድ ላይ ተቀናቃኙን ቼልሲ አስተናግዶ 2 ለ 0 በመርታት የዋንጫ ፉክክሩ ላይ ጉጉት ጨምሮበታል፡፡

ከአምስት አመታት በፊት ሊቨርፑል ዋንጫውን ለማንሳት በተቃረቡበት ሰሞን፤ ያኔ ሰማያዊዎቹ በአሰልጣኝ ዦሴ ሞሪንሆ እየተመሩ ቀያዮቹን 2 ለ 0 በማሸነፍ ዋንጫው ከማንሳት አግደዋቸው የነበረ በመሆኑ አሁንም ታሪክ እንዳይደገም የተፈራ ቢሆንም የመርሲ ሳይዱ ቡድን ግምቱን ፉርሽ አድርጓል፡፡

በሁለቱ ቡድኖች ግጥሚያ የመጀመሪያው አጋማሸ ግብ ያልተስተናገደበት ቢሆንም የቀያዮቹ የበላይነት እና ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመድረስ እና ሙከራዎችን በማድረግ የተሻሉ ነበሩ፡፡ የመሀመድ ሳላህ እና ሳዲዮ ማኔ ያደረጓቸው የግል ሙከራዎችም ግብ መሆን የሚችሉ ነበሩ፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ላይ ሴኔጋላዊው ኮከብ ሳዲዮ ማኔ በግንባሩ በመድፈቅ ቀያዮቹን ቀዳሚ መሪ ሲያደርግ ፤ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሌላኛው አፍሪካዊ  መሀመድ ሳላህ ከ24 ሜትር አካባቢ ርቀት ላይ አክርሮ የመታት ኳስ የግቡ ቀኝ ኮርነር ላይ በመረፍ ሌላኛዋ ግብ ሁና ተመዝግባለች፡፡

ሳላህ በሊጉ ያስቆጠራቸውን የግብ መጠንም ወደ 19 በማድረስ ከአጉዌሮ ጋር እኩል መሆን ችሏል ፤ ማኔ ደግሞ ትናንት 18ኛ ጎሉን አስቆጥሯል፡፡

ሰማያዊዎቹ ተከታታይ ግቦችን ካስተናገዱ በኋላ ግብ ለማስቆጠር በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚቸው የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ ቢችሉም ሙከራቸው ፍሬ ማፍራት አልቻለም፡፡

በተለይ ኢዲን ሀዛርድ ያደረጋቸው ሁለት ተከታታይ የግብ ዕድሎች ቡድኑን አቻ ማድረግ የሚችሉ ቢሆንም በቋሚ የግቡ ፖል እና በግብ ጠባቂው አሊሰን ቤከር ሳይቆጠሩ ቀርተዋል፡፡

ባለሜዳዎቹም ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ባይሳካም፤ ከሰዓታት በፊት በተቀናቃኛቸው ማንችስተር ሲቲ ተነጥቀው የነበረውን የሊጉን የደረጃ ሰንጠራዥ መሪነት መልሰው በ85 ነጥብ ተረክበዋል፡፡

ቀን ማንችስተር ሲቲ ወደ ለንደን ተጉዘው ክሪስታል ፓላስ ላይ የ 3 ለ 1 ድል አሳክተዋል፡፡ እንግሊዛዊው ራሂም ስተርሊንግ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ፣ ጋብሪዬል ጄሱስ ተጨማሪዋን ግብ ከመረብ አገናኝቷል፡፡

ሊጉ ሊጠናቀቅ የአራት ጨዋታዎች ዕድሜ በቀሩበት ጊዜ ሲቲ ከጎረቤት ማንችስተር ዩናይትድ ጋር ተስተካካይ አንድ መርሀግብር ይቀረዋል፤ ሌሎቹ ደግሞ ቶተንሃም፣ በርንሌ፣ ሌስተር እና ብራይተን ናቸው፡፡

የሊቨርፑል ቀሪ ተጋጣሚዎች ካርዲፍ ሲቲ፣ ሀደርስፊድ፣ ኒውካስትል እና ወልቭስ ሲሆኑ ከማ.ሲቲ አንፃር ሲታዩ የቀያዮቹ ተጋጣሚዎች ቀላል የሚባሉ ናቸው፡፡

ዛሬ ምሽት 4፡00 የሳምንቱ መደምደሚያ ግጥሚያ ሲጀመር፤ የሰሜን ለንደኑ አርሰናል ወደ ዲን ኮርት አቅንቶ ዋትፎርድን ይጎበኛል፡፡

በምሽቱ ግጥሚያ ባለሜዳዎቹ የዦሴ ሆሌባስ፣ ዶሚንጎስ ኩይና እና ቶም ክሌቨርሊ ግልጋሎት አያገኙም ተብሏል፡፡

በመድፈኞቹ በኩል ተከላካዩ ሶቅራቲስ ፓፓስታቶፑሎስ የተመለከታቸው የቢጫ ካርዶች ብዛት 10 በመድረሱ የሁለት ጨዋታዎች ቅጣቱን በዚህ ይጀምራል፤ ግራኒት ዣካም ቢሆን ለጨዋታው ዝግጁ ስለመሆኑ እርገጠኛ መሆን አልተቻለም፡፡  

በምሽቱ ጨዋታ የሰሜን ለንደኑ ቡድን ድል የሚቀናው ከሆነ ነጥቡን ወደ 66 ከፍ በማድረግ ከቼልሲ ጋር በማስተካከል፣ ባለው የግብ ክፍያ በልጦ አራተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ይችላል፡፡

ቅዳሜ ዕለት ቶተንሃም ሆትስፐርስ በሉካስ ሞራ ሀትሪክ እና ዋንያማ ተጨማሪ ጎል በሜዳው ሀደርስፊልድን 4 ለ 0 በመርታት በ67 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ማንችስተር ዩናይትድ በኦልድ ትራፎርድ በዌስት ሃም በተፈተነበት ግጥሚያ በፖል ፖግባ ሁለት የፍጹም ቅጣት ምት ጎሎች ታግዞ 2 ለ 1 በመርታት 64 ነጥቦችን ሰብስቦ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተሰይሟል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *