በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መከላከያ ይጫወታሉ
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መከላከያ ይጫወታሉ
የሊጉ የ10ኛ ሳምንት መርሃግብር ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ ይከናወናሉ፡፡ ዛሬ ሶስት ጨዋታዎች ሲደረጉ በአዲስ አበባ ስታዲም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መከላከያ 10፡00 ሰዓት ላይ ይገናኛሉ፡፡ ጨዋታው በኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው ይመራል ተብሏል፡፡
ክልል ላይ ሀዋሳ ከነማ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ስታዲየም ከ መቐለ 70 እንደርታ እንዲሁም በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከነማ በተመሳሳይ 9፡00 ይከናወናሉ፡፡
ነገ ደግሞ አራት ጨዋታዎች ክልል ላይ በሚገኙ ስታዲየሞች ሲከናወኑ፤ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ቡና ወደ ሀዋሳ አቅንቶ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ስታዲየም ከ ሲዳማ ቡና ጋር ይፋለማል፡፡ ኢንተርናሽናል አርቢትር አማኑኤል ኃይለ ስላሴ ደግሞ ጨዋታውን በዳኝነት ይመሩታል፡፡
ባህር ዳር ላይ ባህር ዳር ከነማ ከ ደደቢት ይጫወታሉ፤ ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ከ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሲጫወቱ ሽረ ላይ ስሑል ሽረ ከ ደቡብ ፖሊስ ይገናኛሉ፡፡
ሁሉም ግጥሚያዎች በተመሳሳይ 9፡00 ይደረጋሉ፡፡
በ10ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃግብር ጅማ አባ ጅፋር ከ ፋሲል ከነማ ሊደረግ የነበረው ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ከሞሮኮው ሀሳኒያ አጋርዲን ጋር የሚጫወት በመሆኑ ወደ የካቲት 17 ተገፍቷል::
በሊጉ የደረጃ ሰንጠራዥ ኢትዮጵያ ቡና በ18 ነጥቦች ቀዳሚ ነው፤ ሀዋሳ ከነማ በ17 ይከተላል፤ ሲዳማ ቡና በ13 ነጥብ ሶስተኛ እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ፋሲል ከነማ፣ ባህር ዳር ከነማ እና ወልዋሎ በዕኩል 12 ነጥቦች በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከ4-7 ያለውን ደረጃ ተቆናጥጠዋል፡፡
የሰዲማ ቡናው አጥቂ አዲስ ግደይ በሰባት ጎሎች ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን ይመራል፡፡