በኢትዮጵያ ከ100 ሺህ ሰዎች አምስት ሰዎች በወባ በሽታ ሕይወታቸው እያለፈ መሆኑን ተገለጸ::
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2013 በኢትዮጵያ ከ100 ሺህ ሰዎች አምስት ሰዎች በወባ በሽታ ሕይወታቸው እያለፈ መሆኑን ተገለጸ::የወባ በሽታ ስርጭት ተመልሶ ማንሰራራቱን የጤና ሚኒስቴር አስታዉቋል፡፡ባለፉት ሁለት ዓመታት የወባ በሽታ ስርጭት ተመልሶ እየተንሰራራ መምጣቱን የገለጸዉ ሚኒስቴሩ ፤በሽታውን ለመከላከል አመራሩ፣ ህብረተሰቡና የጤና ባለሙያው በትኩረት እንዲሰሩም ተጠቁሟል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጄ ድጉማ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ”የወባ ሳምንት ” ሲከበር እንደገለጹት፤ በአገሪቱ የወባ በሽታን ለመከላከል ስኬታማ ስራዎች ተከናውነው ውጤቶች ቢመዘገቡም ከሁለት ዓመታት ወዲህ በሽታው መልሶ የመሰራጨት ሁኔታ አሳይቷል።እንደሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ የወባ በሽታ መከላከያ ከሆኑት መንገዶች አንዱ የአልጋ አጎበሮችን በአግባቡ መጠቀም ቢሆንም ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች አጎበሮችን ጥቅም ላይ የሚያውሉ ነዋሪዎች ከ60 እስከ 70 በመቶ አይበልጡም።
በመሆኑም ይህንን ቁጥር እስከ 95 በመቶ ለማድረስ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልገ ገልጸው፣ በተለይ የሚያጠቡና ነፍሰጡር እናቶችን ጨምሮ ሕፃናት ካልጋ አጎበር ውጭ እንዳይተኙ ማድረግ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡በአሁኑ ወቅት በወባ በሽታ መያዝ ብቻ ሳይሆን የሚሞቱ ሰዎችም ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ጠቁመው፣ ከ100 ሺህ ሰዎች አምስት ሰዎች ሕይወታቸው እያለፈ መሆኑን ተናግረዋል።የወባ ስርጭትን ለመከላከል በአሁኑ ወቅት ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸው ለእዚህም በኦሮሚያ ክልል 3 ዞኖች በሚገኙ 68 ወረዳዎች ወባ የማጥፋት ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።