በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ፒ.ኤስ.ጂ እና ሮማ አሸንፈዋል
በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ፒ.ኤስ.ጂ እና ሮማ አሸንፈዋል
የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ትናንት ምሽት ተጀምረዋል፡፡ በምሽቱ
የፈረንሳዩ ፒ.ኤስ.ጂ ወደ እንግሊዝ አቅንቶ በኦልድ ትራፎርድ ማንችስተር ዩናይትድ 2 ለ 0 በመርታት ወደ ቀጣዩ የሩብ ፍፃሜ የማለፍ ዕድሉን አስፍቷል፡፡ ያለ ኔይማር እና ካቫኒ ወደ ሜዳ የገባውን የፓሪስ ቡድን አሸናፊ ያደረጉ ግቦች ደግሞ ፕሬስኔል ኪምፔምቤ እና ክልያን ምባፔ በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ከመረብ አገናኝተዋል፡፡
ፖል ፖግባ በ89ኛው ደቂቃ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል፡፡
አሰልጣኝ ኦሌ ጉናር ሶልሻዬርም የመጀመሪያ ሽንፈት ገጥሞታል፤ ቡድኑ የመልሱን ጨዋታ ፓርክ ደ ፕረንስ ላይ ሲያደርግ ከ2 ለ 0 ባለፈ ጎል ድል ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
ሌላኛው በምሽቱ የተከናወነው ግጥሚያ ደግሞ በስታዲዮ ኦሎምፒኮ፤ ሮማ የፖርቱጋሉን ፖርቶ አስተናግዶ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ድል አድርጓል፡፡ ለጣልያኑ ቡድን ሁለቱን የድል ግቦችን ያስቆጠረው ወጣቱ ጣሊያናዊ ኒኮሎ ዛኒዮሎ ሲሆን አድርያን ሎፔዝ ለፖርቶ ለመልሱ ጨዋታ ተስፋ የሰጠች ግብ ከመረብ አገናኝቷል፡፡
የመልስ ግጥሚያዎች ከሶስት ሳምንታት በኋላ የሚከናወኑ ይሆናል፡፡
ዛሬ ምሽት በተመሳሳይ 5፡00 ሰዓት ሁለት ጨዋታዎች ሲከናወኑ፤ ቶተንሃም ከ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ እና አያክስ ከ ሪያል ማድሪድ ይፋለማሉ፡፡