በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ትልቁ ፈተና የዋጋ ግሽበት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ::
አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2014 የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ስድት ወራት በጦርነት፣ በኮቪድ-19 እንዲሁም በተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ከፍተኛ ፈተና ደርሶበታል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ በዚህም ህዝቡ ገዝቶ መብላት እስኪቸገር ድረስ በኑሮ ውድነት ተሰቃይቷል በማለትም የችግሩን አስከፊነት አስታውሰዋል፡፡
የዋጋ ግሽበት በመላው ዓለም እየጨመረ መሆኑ ቢታወቅም እንደኛ ድሃ በሆኑ ሀገራት ግን ችግሩ ሰፊ ጉዳት ያደርሳል ብለዋል፡፡ለዋጋ ግሽበቱ መባባስ በርካታ ምክንያቶችን የሚጠቀሱ ሲሆን በዋናነት የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ነጋዴው የሸቀጥ ዋጋ ይጨምራል በሚል ምርት የመደበቅ ተግባር ላይ መሰማራቱና አቅም ያላቸው ሸማቾች በተመሳሳይ ስጋት በርካታ ምርቶችን የመግዛትና የማከማቸት ፍላጎት ማሳየታቸው ነው ተብሏል፡፡
ይህም በገበያ ላይ ከፍተኛ የአቅርቦት እጥረት እንደሚፈጥርና በዚህም የዕለት ጉርሱን ለማግኘት የሚሯሯጠው የህብረተሰብ ክፍል ለከፍተኛ ችግር እንደሚዳረግ ጠቅሰዋል፡፡ ይህን ችግር ለመቋቋም የግብርና ምርትን ማሳደግና ህገወጥነትን በጋራ መከላከል ሁነኛ መፍትሄ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
መንግስት ከፍተኛ የውጭ እዳ ያለበት መሆኑና ወደ ሀገር የሚገቡ ሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ይበልጥ ፈተና ሆኗል ሲሉም አብራርተዋል፡፡