በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አመርቂ ውጤት አምጥተዋል
ዕሁድ በፈረንሳይ ፓሪስ ማራቶን በወንዶች፡ ኢትዮጵያውያኑ አብርሃ ሚላው 2፡ 07፡ 25 እና አሰፋ መንግስቱ 2፡ 07፡ 25 አንደኛ እና ሁለተኛ ሲወጡ ኬንያዊው ፖል ሎንያንጋታ 2፡ 07፡ 29 ሶስተኛ ደረጃ ይዘዋል፡፡
በሴቶች ገለቴ ቡርቃ በ2፡ 22፡ 47 ቀዳሚ ስትሆን፤ አዝመራ ገብሩ 2፡ 22፡ 52 ሁለተኛ እንዲሁም አዝመራ አብርሃ በ2፡ 23፡ 35 ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቅቀዋል፡፡
ኤርትራዊው አትሌት መርሃዊ ከሰተ በ2፡ 09፡ 06 ጊዜ አሸናፊ በነበረበት የኦስትሪያ የሊዝ ማራቶን ውድድር ኢትዮያዊው ጋዲሳ አራተኛ ደረጃ ላይ ጨርሷል፡፡
በፖላንድ መዲና ዋርሳው ማራቶን ደግሞ በወንዶች ረጋሳ ምንዳዬ በጂጋ በ2፡ 09፡ 42 ሰዓት አሸናፊ ሲሆን ኬንያዊው እዝኬል ኬምቦይ በ2፡ 09፡ 49 እና ወርቅነህ አቦዬ በ2፡ 10፡ 42 ሶስተኛ ሁኖ አጠናቅቋል፡፡
ኔዘርላንድስ ላይ በኢንስቼድ ማራቶን በሴቶች ኬንያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ አራት ተከታትለው በመግባት ሲያሸንፉ፤ ኢትዮጵያውያኑ ዘውድነሽ አየለ፣ ገዳምነሽ መኳንንት እና አስመራወርቅ በቀለ ከአምስት እስከ ሰባት ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቅቀዋል፡፡
በቻይና ውሃን ማራቶን በሴቶች ፋንቱ ጀማል 2፡ 28፡ 25 1ኛ፤ ፀሃይ ማሩ በ2፡ 28፡ 49 2ኛ ሲሆኑ በወንዶች በላቸው አለማየሁ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቅቋል፡፡
በሴኔጋል ዳካር ማራቶን ኢትዮጵያዊው ሂሪቦ ሻኖ 2፡ 14፡ 14 ጊዜ አሸንፏል፡፡
በፈረንሳይ የላክ አኔሲ ማራቶን በወንዶች ይከበር ባያብል ገሰሰ እና በሴቶች ገነት ሃቤላ ተፎካካሪዎቻቸውን አስከትለው ገብተዋል፡፡ ጫልቱ ዲዳ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡
ጣሊያን ላይ በነበረው የሌክ ማጎሬ ግማሽ ማራቶን በሴቶች መሰረት ገዛሃኝ ቀዳሚ ሁና አጠናቅቃለች፡፡
በፖዝናን ግማሽ ማራቶን ሲያስ ምስጋናው በ1፡ 02፡ 29 ጊዜ አንደኛ ሁኗል፡፡
በቦስተን 5 ኪ.ሜ ሃጎስ ገብረሂወት፣ በሞሮኮ ታርፋያ 8 ኪ.ሜ ጠጄ መኮነን አሸናፊ ሁነዋል፡፡