በመጪው የገና በዓል ኤሌክትሪክ እንዳይቋረጥ በቂ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ
በበዓላት በሚኖረዉ ከፍተኛ የሀይል ፍላጎት የተነሳ ሊያጋጥም የሚችለውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ ለማስቀረት በቂ ዝግጅት ማድረጉን ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
አገልግሎቱ ለአርትስ ቲቪ በላከው የፕሬስ መግለጫ እንዳስታወቀው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ጋር በመተባበር ለሚፈጠረው የኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ አፋጣኝ መፍትሔ የሚሰጥ የጋራ ተጠባባቂ ኮሚቴ አቋቁሜያለሁ ብሏል።
ችግሩ ይከሰትባቸዋል የተባሉ አካባቢዎችን የበዓሉ ቀን ከመድረሱ በፊት መለየቱንና የመልሶ ግንባታ፣ አቅም የማሳደግ፣ የጭነት ማመጣጠንና የቅድመ መከላከል ጥገና ሥራዎች እያከናወነ መሆኑንም ተናግሯል።
ከዚህ አልፎ በበዓሉ ቀንም የሃይል መቆራረጥ ከተፈጠረ ችግሩን በአፋጣኝ ለመፍታት የሚያስችሉ የአስፈላጊ የግብዓት አቅርቦት መሟላቱም ተጠቁሟል።
ፋብሪካዎችና ሌሎች የከፍተኛና የመካከለኛ ኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች ከታህሳስ 28 ቀን 2011 ዓ.ም ንጋት 12፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ንጋት 12፡00 ሰዓት ድረስ ኃይል ቀንሰው እንዲጠቀሙ ትብብር ጠይቋል።
በኅብረተሰቡ በኩልም ኤሌክትሪክ መጠቀሚያ ሰዓትን በምሽት እና ሌሊት በማድረግ የሃይል እጥረትን ለመከላከል የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፏል።