ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ እና ሰር ሞ ፋራህ እየተወዛገቡ ነው
በሩጫው ዘርፍ ስማቸውን ካስጠሩት መካከል ሁለቱ አትሌቶች የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ቀልብ ስበዋል፡፡
የቀድሞው የረዥም ርቀት ንጉስ ኢትዮጵያዊው ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ እና ብሪታኒያዊው ሰር ሞ ፋራህ ከሩጫው ፉክክር ውጭ በሆነ ጉዳይ መረር ያለ እሰጣ ገባ ውስጥ ተገናኝተዋል፡፡ ስርቆት እና ያልተከፈለ የሆቴል ሂሳብ ደግሞ የውዝግቡ ነጥቦች ናቸው፡፡
ይህ ነገር የተሰማው የለንደን ማራቶን ሊካሄድ የጥቂት ቀናት ዕድሜ በቀረበት ወቅት ነው፡፡
የአራት ጊዜ የኦሊምፒክ ሜዳሊያ ባለድሉ ብሪታኒያዊው አትሌት፤ ለውድድሩ ይረዳው ዘንድ የዝግጅት ጊዜውን በኢትዮጵያ በኃይሌ ንብረት በሆነው እና ከአዲስ አበባ አቅራቢያ በሚገኘው ያያ ቪሌጅ ውስጥ በሳለፍነው የመጋቢት ወር መጨረሻ አካባቢ አድርጓል፡፡
ፋራህ የዕሁዱን የለንደን ማራቶን በድል ለመወጣት እያለመ ባለበት ሰዓት ከውድድሩ አስቀድሞ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው የዝግጅት ወቅት በሆቴል ክፍሉ ውስጥ ባጋጠመው ስርቆት ኃይሌ ንብረቴን ለማስመለስ ትብብር አላደረገልኝም ሲል ወቀሳ አሰምቷል፡፡
ሞ ፋራህ የደረሰበትን በደል ለኃይሌ በፅሁፍ መልዕክት እንዳስረዳ እና ትብብር እንዲያደርግለት እንደጠየቀ፤ ነገር ግን ተገቢው ምላሽ እንዳልተሰጠው ለመገናኛ ብዙሃን አስረድቷል፡፡
ፋራህ ተሰረኩ ብሎ የተናገረው ከባለቤቱ ታኒያ የተበረከተለት 2500 ፓውንድ አካባቢ የሚያወጣ ሰዓት፤ ሁለት ስልኮች እና ገንዘብ ነው፡፡
አትሌቱ እንደሚለው ‹‹አንድ ሰው ከእንግዳ ተቀባዮ ባለሙያዎች ቁልፍ ወስዶ ያዘውን ክፍል በመክፈት ገንዘቡን፣ ምርጡን ሰዓቱን እና ሁለት ስልኮች ወስዷል›› ሲል አብራርቷል፡፡
የኦሊምፒክ ድልን ከአንድም ሁለቴ ያሸነፈው ኃይሌ በበኩሉ ለአርትስ ስፖርት በሰጠው ምላሽ የፋራህን ወቀሳ ወይንም ስም ማጥፋት በማጣጣል፤ ይባሱኑ ያለበትን የሆቴል ሂሳብ እንዳልከፈለም ተናግሯል፡፡ እንዳውም ከፋራህ በደረሰው ጥቆማ አስፈላጊውን ትብብር እንዳደረገለት እና ሞ ለሚያቀርባቸው ክሶች ምስክርም ሆነ ማስረጃ እንዳላቀረበ ተናግሯል፡፡
ኃይሌ በደረሰው ጥቆማ መሰረት የሞ ፋራህን ጉዳይ ለማጣራት ምርመራ ቢደረግም ስለስርቆቱ ምንም አይነት ማረጋገጫ እንዳልተገኘ ጠቁሟል፡፡
‹‹ጉዳዩንም ወደ አደባባይ ከመውጣቱ በፊት፤ እዛው ለመፍታት ያደረገው ጥረት እንደልተሳካለት የሚናገረው ኃይሌ፤ ፋራህ ጉዳዩን ለሚዲያ እንደሚያወጣው እንዳስፈራራው አስታውቋል፤ እናም እንደፎከረው አደረገው›› ሲል ጨምሯል፡፡
በቀጣይም በተደረገው የስም ማጥፋት የሚኖሩ ምላሾች እና ያልተከፈለ የሆቴል ወጪዎችን ለማስከፈል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በተመለከተ ጠይቀነው ‹‹ሞ እዚህ ፕላኔት ላይ ስላለ አያሳስብም›› በቀጣይ የሚታይ መሆኑን ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ ለአርትስ አስረድቷል፡፡