ስድስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ለጨረታ ሊቀርቡ መሆኑ ተነገረ።
ስድስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ለጨረታ ሊቀርቡ መሆኑ ተነገረ
በኢትዮጵያ መንግስትና በግል አጋርነት የሚተገበሩ ስድስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናታቸው ተጠናቆ ለጨረታ ሊቀርቡ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚንስትር ዴኤታው ዶክተር ተሾመ ታፈሰ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ያቋቋመው ቦርድ በመንግስትና የግል አጋርነት ይተገበራሉ ብሎ ከለያቸው 16 ፕሮጀክቶች ውስጥ አስራ ሶስቱ የኃይል አቅርቦት ፕሮጀክቶች ሲሆኑ ሶስቱ የትራንስፖርት ፕሮጀክቶች ናቸው ብለዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ በኃይል አቅርቦት ከተለዩ 13 ፕሮጀክቶች መካከል 798 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጩ ስድስት ፕጀክቶች የአዋጭነት ጥናታቸው ተጠናቋል። ፕሮጀክቶቹ ወደ ጨረታ ሂደት የሚያስገባቸው ተግባርም እየተከናወነ ሲሆን ተግባራዊ ለማድረግም 795 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል።
ፕሮጀክቶቹም በአፋር፣ ሶማሌ፣ ኦሮሚያና በትግራይ የሚተገበሩ ሲሆን ሙሉ ወጪውን የሚሸፍነው ጨረታውን የሚያሸንፈው የግል ባለሃብት መሆኑም ተጠቅሷል።
በአፋርና በሶማሌ የሚተገበሩት ዲቼኤቶና ጋድ የተሰኙት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ከመንግስት ጋር ለሚሰራ የግል ባለሃብት ጨረታ የሚቀርቡ ሲሆን ቀሪዎቹ በሂደት የሚከናወኑ መሆኑንም ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር ተሾመ ተናግረዋል ።
መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ ትልቅ ትኩረት መስጠቱን ገልጸው ለፕሮጀክቶቹ አፈፃፀም የህግና ተቋማዊ ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
በፕሮጀክቱ ለመሳተፍ በርካታ የግል ባለሃብቶች ፍላጎት ማሳየታቸውንም ተገልጿል።