ሲዳማ ቡና የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ መሪ ሆነ
ሲዳማ ቡና የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ መሪ ሆነ
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ወይንም የ15ኛ ሳምንት ግጥሚያዎች ከትናንት ቀጥለው ዛሬም ተከናውነዋል፡፡
ዛሬ በክልል ስታዲየሞች ሶስት ያህል ጨዋታዎች የተከናወኑ ሲሆን ሀዋሳ ላይ የአምናውን የፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮን፤ ጅማ አባ ጅፋር ያስተናገደው ደቡብ ፖሊስ ግማሽ ደርዘን ግብ አስቆጥሮ 6 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት ረምርሞታል፡፡
ለደቡቡ ቡድን ይተሻ ግዛው፣ ዘላለም ኢሳያስ እና ሄኖክ አየለ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ግቦችን አስቆጥረው ክለባቸው የውድድር ዓመቱን ሶስተኛ ድል እንዲያሳካ አግዘዋል፡፡ ጅማዎች በባዶ ከመሸነፍ ያዳነቻቸውን ግብ በአስቻለው ግርማ አማካኝነት አግኝተዋል፡፡
ደቡብ ፖሊስ ድሉን ተከትሎ የመጀመሪያውን ዙር በ11 ነጥቦችና እና 3 የግብ ዕዳዎች አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ እዛው ወራጅ ቀጠና ውስጥ ተገኝቶ 14ኛ ላይ ተቀምጧል፡፡
በተመሳሳይ ሰዓት ደግሞ ወደ ጎንደር ያቀናው የትግራዩ ስሑል ሽረ ፋሲለደስ ለይ በፋሲል ከነማ 3 ለ 0 ተረትቷል፡፡ ዓፄዎቹ አሸናፊ ያደረጓቸውን ጎሎች ሱራፌል ዳኛቸው ሁለት እና ኢዙ አዙካ ተጨማሪ ግብ ከመረብ አገናኝተዋል፡፡ ፋሲል በደረጃ ሰንጠራዡ አምስተኛ ላይ ጉብ ብሏል፡፡ በአንፃሩ የሽረው ቡድን ወራጅ ቀጠና ውስጥ አንድ ደረጃ ዝቅ ብሎ በ11 ነጥቦች 15ኛ ላይ ተገኝቷል፡፡
መቐለ ላይ በትግራይ ስታዲየም በወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ሲዳማ ቡና መካከል የተካሄደው ጨዋታ ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቅቋል፡፡ ሲዳማ ሶስት ነጥብ የማግኘት ዕድሉ ቢከሽፍበትም ባገኛት አንድ ነጥብ ታግዞ በ27 ነጥብ ወደ ሊጉ መሪነት ከፍ ብሏል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በ26 ነጥብ መቐለን በግብ ክፍያ በመብለጥ ሁለተኛ ሁኗል፡፡
ትናንት በተደረጉ የሊጉ ጨዋታዎች ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ቅዱስ ጊዮርጊስን 2 ለ 0 ሲረታ፤ ሀዋሳ ከተማ ደደቢትን 1 ለ 0 አሸንፏል፡፡ ባህር ዳር ከነማ ደግሞ ከአዳማ ከተማ ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡
ነገ የሳምንቱ የማጠናቀቂያ ሁለት ጨዋታዎች ሲካሄዱ፤ የትግራዩ መቐለ 70 እንደርታ ወደ ምስርቅ ኢትዮጵያ አምርቶ ድሬዳዋ ስታዲየም ላይ ከድሬዳዋ ከነማ ጋር 9፡00 ሲል ይፋለማል፡፡ መቐለ ድል የሚቀናው ከሆነ የሊጉን መሪነት ከሲዳማ ቡና ይረከባል፤ ያኔ ደግሞ ጊዮርጊሶች ወደ ሶስተኛ ደረጃ የሚወርዱ ይሆናል፡፡
በአዲስ አበባ ስታዲየም ደግሞ በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ምክንያት ከዕሁድ ወደ ማክሰኞ የተዘዋወረው የመከላከያ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ 10፡00 ላይ ይከናወናል፡፡ ባለሜዳ ሁኖ ወደ ሜዳ የሚገባው የጦሩ ቡድን ትግራይ ላይ ይዞት የተመለሰውን ድል ለማስቀጠል እንዲሁም ቡናማዎቹ ከተከታታይ ሽንፈት ለመውጣት የሚያደርጉት ተጠባቂ ግጥሚያ ነው፡፡