loading
ሞስኮን ያልበረገራት የምእራባዊያን የነዳጅ ማእቀብ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2014 በሩሲያ ላይ የተጣለው የነዳጅ ግብይት ማእቀብ ግቡን እዳልመታ የሚገልጽ አዲስ ሪፖርት ይፋ ሆነ፡፡ ሪፖርቱ ፕሬዚዳንት ቭላደሚር ፑቲን ጦራቸውን ወደ ዩክሬን ባዘመቱ በ100 ቀናት ውስጥ ሞስኮ ከነዳጅ ሽያጭ 98 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን ይገልጻል፡፡ ይህን ሪፖርት ይፋ ያደረገው ተቀማጭነቱ ፊንላንድ የሆነ በኢነርጂና ንጹህ አየር ላይ ምርምር የሚያደርግ ገለልተኛ ተቋም ነው ተብሏል፡፡


እንደተቋሙ ማብራሪያ ከሆነ አሜሪካ በአውሮፓዊያንና በሩሲያ መካከል ያለው የነዳጅ ግብይት እንዲቆም ከባድ ማእቀብ ብትጥልም አሁን ሩሲያ አገኘችው ከተባለው ገቢ 61 በመቶው ወደ አውሮፓ ከተላከ ነዳጅ ነው፡፡ በነዚህ የጦርነት ወራት ከፍተኛ ነዳጅ ከሩሲያ ካስገቡ የአውሮፓ ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ ጀርመን ስትሆን ጣሊያን፣ ኔዘርላንድስ፣ ቱርክ፣ ፖላንድና ፈረንሳይም በማእቀብ ውስጥ ከሞስኮ ነዳጅ በብዛት የገዙ ሀገራት ሆነው ተመዝግበዋል፡፡


የሩሲያ የነዳጅ መላኪያ ዋጋ ካለፈው ዓመት በ60 በመቶ ገደማ ቢጨምርም እንደ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ህንድና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የመሳሰሉ ሀገራት የግዥ መጠናቸውን ማሳደጋቸው ተሰምቷል፡፡ ይህን የሰማቸው ኬቭ በበኩሏ ምእራባዊያን በአንድ በኩል የጦር መሳሪያ ድጋፋቸው እንዳይቋረጥ ጎን ለጎን ደግሞ በሩሲያ ላይ የሚጣለው ማእቀብ እንዲጠነክር ጠይቃለች ሲል አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ በሩሲያ የነዳጅ ምርት ላይ የጣሉት ማእቀብ ከባድ ነው ብለው ቢያስቡም ውጤቱ ግን እንደታሰበው ሳይሆን በተቃራኒው እየሄደ መሆኑን ጥናቱን ዋቢ አድርገው ተንታኞች ይናገራሉ፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *