loading
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የላሊበላን ቅርስ ከተጋረጠበት አደጋ ለመታደግ ልንረባረብ ይገባል አሉ

በላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት እድሳት  ዙሪያ ለመወያየት ከላሊበላ ከተማ የመጡ ኮሚቴዎች ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መወያየታቸውን ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

የላሊበላ አብያተክርስቲያናት አስተዳዳሪ ብፁዕ አባ ፅጌ ስላሴ እንደተናገሩት አብያተክርስቲያናቱ የመፍረስ አደጋላይ መሆናቸው በተደጋጋሚ መነገሩን ተከትሎ የከተማዋን ወጣቶች ፣ከደብሩ አስተዳዳሪዎች እና የከተማዋ ከንቲባ ያካተተ ኮሚቴ ከምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ጋር ባደረገው ውይይት ቅርሱ በፍጥነት በሚታደስበት እና መጠለያዎቹ በሚነሱበት አግባብ ላይ መወያየታቸውን ገልፀዋል፡፡

አቶ ደመቀ  በቅርሶቹ ዙሪያ በቅርቡ ከሃገር ውስጥ እና ከውጭ ምሁራንን  እና የሚመለከታቸውን አካላት የሚያሳትፍ  ሃገር አቀፍ መድረክ ተዘጋጅቶ እንደሚመከርበት እና የተባለው ገንዘብ  ባይገኝ  እንኳን በዚህ አመት መጠለያዎቹ ተነስተው እድሳቱ እንደሚደረግ ቃል መግባታቸውን ነው አስተዳዳሪው የገለፁት፡፡

ላሊበላን ሰርቶ ያስረከበን ትውልድ አካል እስከሆንን ድረስ በአሁን ጊዜ ቅርሱ ከተጋረጠበት አደጋ ለመታደግ ትውልዱ በሃላፊነት መረባረብ እንደሚጠበቅበት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የላሊበላ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃብታሙ ማሞ በበኩላቸው ከዚህ ቀጥሎ ኮሚቴው አዲስ አበባ በሚኖረው ቆይታ  ከ ኢዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር በቅርሶቹ ዙሪያ ይወያያል ብለዋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *