ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ አራት የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታን አስጀመሩ
ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ አራት የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታን አስጀመሩ
አርትስ 18/02/2011
ዛሬ በአዲስ አበባ ግንባታቸው በይፋ የተጀመሩት የመንገድ ፕሮጀክቶች ከራስ ደስታ ሆስፒታል- ቀጨኔ መድሃኔዓለም 8 ቁጥር ማዞሪያ አንዱ ነው።
በተጨማሪም ከመገናኛ- ውሃ ልማት- ግብርና ሚኒስቴር መጋዘን- አዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ዋና መስሪያ ቤት- ወረዳ 17 ጤና ጣቢያ እንዲሁም ቦሌ አያት ሳይት አራት እና ቦሌ አያት 1፣ 2፣ 3፣ 4 ናቸው።
አዳዲስ የሚጀመሩት የመንገድ ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ 15 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና የተለያየ የጎን ስፋት ሲኖራቸው 834 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብም ወጪ እንደሚደረግባቸው የከንቲባ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ከራስ ደስታ ሆስፒታል- ቀጨኔ መድሀኔዓለም- 8 ቁጥር ማዞሪያ የመንገድ ፕሮጀክት 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመትና ከ20 እስከ 40 ሜትር ስፋት ኖሮት የሚገነባ መንገድ መሆኑም ተነግሯል።
ፕሮጀክቱ የተጀመረውም ምክትል ከንቲባው ከሁሉም ክፍለ ከተማ ወጣቶች ጋር ባደረጉት ውይይት በተለይም በጉለሌ ክፍለ ከተማ እንደ አንድ ችግር የተነሳው የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄ መሆኑን ተከትሎ ነው ተብሏል።
የመንገድ ፕሮጀክቱን የግንባታ ስራ ማርካን ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተባለ ሀገር በቀል ስራ ተቋራጭ ከ204 ሚሊየን ብር በላይ የሚያከናውን መሆኑም ተገልጿል።
የአራቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ የወሰን ማስከበር ስራን ጨምሮ በሁለት ዓመት ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም የከንቲባ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።