መንግስት 41ሺህ 485 ዜጎችን ከሳዑዲ አረቢያ መመለሱን ገለጸ::
አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 21፣ 2013 የኢትዮጵያ መንግስት 80 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 41ሺህ 485 ዜጎችን ከሳዑዲ አረቢያ እንዲመለሱ ማድረጉን የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
በብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አማካኝነት በአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ምላሽ ማእከል ከሳውዲ አረቢያ ተመላሽ ወገኖችን በመቀበል እና በማስተናገድ እንዲሁም ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ በማድረግ እየሰራ እንደሆነ የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ገልጸዋል።
በርካታ ዜጎች በሁለቱ ሀገራት ስምምነት መሰረት በኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ አየር መንገዶች በመታገዝ መጓጓዝ ችለዋል።
ለተመላሾች ጊዜያዊ ማቆያ ስፍራ በማመቻቸት፣ የአልባሳት ምግብ እና የመጠጥ አቅርቦት፣ የመኝታ ፍራሽ እንዲሁም የትራንስፖርት አቅርቦት በማከናወን ረገድ ብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በኃላፊነት የማስተባበር ስራ ሰርቷል ብለዋል አቶ ደበበ። ከኮሚሽኑ ጋር የሰላም ሚኒስቴር፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴር፣ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን፣ የሴቶች እና ህፃናት ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ
እየሰሩ ይገኛሉ ሲሉ አቶ ደበበ ተናግረዋል።
በአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ምላሽ ማእከል በሳምንት ሶስት ጊዜ በመገናኘት በዘጠኝ የመቀበያ ጣቢያዎች ከቦሌ ዓለም አቀፍ ጣቢያ በማምጣት የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል ሲሉ ዳይሬክተሩ መግለጻቸውን ኢቢሲ ዘግቧል። ለስደት ተመላሾቹ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደ ዓለም አቀፍ የስደት ተመላሾች ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ተገልጿል። በተለይም ቤተሰብ የሌላቸውን በመደገፍ በኩል ድርጅቱ ያሳየው አጋርነት ሊመሰገን ይገባል ሲሉ አቶ ደበበ ዘውዴ ተናግረዋል።