ልጣን ላይ ያሉትና የቀድሞ የአፍሪካ መሪዎች ለ8ኛዉ የጣና ከፍተኛ የደኅንነት ፎረም ባህር ዳር ከተማ ሊገናኙ ነው
በስልጣን ላይ ያሉትና የቀድሞ የአፍሪካ መሪዎች ለ8ኛዉ የጣና ከፍተኛ የደኅንነት ፎረም ባህር ዳር ከተማ ሊገናኙ ነው።
መሪዎቹ ባህር ዳር የሚገናኙት በአፍሪካ ቀንድ ሁኔታዎች ላይ ለመምከር ነው።
”የፖለቲካ ተለዋዋጭነት በአፍሪካ ቀንድ እና የታዩ የሠላም ጅማሮዎችን ማጎልበት” በሚል መሪ መልክዕት የሚካሄደው ይኸው ፎረም ከሚያዚያ 26-27 ድረስ ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድ ነው ማወቅ የተቻለው።
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ላቀ አያሌዉ እንደተናገሩት ከተማዋ ለምታስተናግደው ለዚህ ለዚህ ከፍተኛ መድረክ ስኬት ቅድመ ዝግጅት እየተካሄደ ነው።
በመስተንግዶ፣ ፀጥታ፣ መጓጓዣ ጽዳትና በሌሎች መስኮች ፎረም አደረጃጀቶች ተዋቅረዉ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው ም/ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት።
ከልሉ በዚህ ፎረም ተሳታፊ ለሚሆኑት እንግዶች በክልሉ ያሉትን የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ጸጋዎች እንደሚያስተዋውቅ ነው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የገለፁት።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አማረ ዓለሙ በበኩላቸው ከተማዋን የቱሪስት መስህቦች ለፎረሙ ታዳሚዎች እናስጎበኛለን ነው ያሉት። “የባህርዳርን ጽዳትና ዉበት በዚህ ከፍተኛ መድረክ ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን” ብለዋል።
በፎረሙ ለሚሳተፉ እንግዶች መቆያ በክልሉ የሚገኙ 28 ሆቴሎች ተመዝነው ደረጃቸዉን እየተጠባበቁ መሆኑን የገለጸው የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከእነዚህ ውስጥ ስድስቱ በባሕር ዳር የሚገኙ እንደሆኑም አመልክቷል።