ለ4 ተከታታይ ዓመታት የተሸለመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ…
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 02፣ 2014የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአራት ዘርፎች የምርጥ የ'ስካይትራክስ የ2021 የአየር መንገድ ሽልማቶች አሸናፊ ሆነ፡፡ አየር መንገዱ እ.አ.አ የ2021 የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ ሽልማትን ጨምሮ ለ4 ተከታታይ ዓመታት ነው የተሸለመው። የአፍሪካ ምርጥ የቢዝነስ ክፍል ሽልማትን ለ3 ተከታታይ ዓመታት፣ የአፍሪካ ምርጥ የምጣኔ ሃብት ክፍልም ለሶስት ተከታታይ ዓመታት አሸንፏል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የ2021 ምርጥ የካቢን ሠራተኞች ሽልማት ማሸነፉ ተገልጿል።
አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ የአየር መንገድ ደንበኞች ምርጫ እ.አ.አ በ2021 ሰባት ደረጃዎችን በማሻሻል ከምርጥ 100 የዓለም አየር መንገዶች 37ኛ ደረጃ መያዙም ተነግሯል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ አየር መንገዱን በስኬት ማስቀጠል ፈታኝ ሥራ እንደነበር ገልጸዋል። ሆኖም እኛ ኢትዮጵያዊያን ተስፋ አልቆረጥንም፤ ለደንበኞቻችን ያለንን ታማኝነት ጠብቀን በረራችንን
በመቀጠላችን ስኬት አስመዝግበናል ብለዋል። ሽልማቶቹ በዓለም ዙሪያ ያለማቋረጥ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የጥረት ማረጋገጫ መሆናቸውንም
ተናግረዋል።
አየር መንገዱ የተጓዦችን ድምጽ በማግኘት የስካይትራክስ ሽልማት አሸናፊ መሆኑ ስኬቱን ያጠናክረዋል ነው ያሉት አቶ ተወልደ። የስካይትራክስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኤድዋርድ ፕሌስቴድ በበኩላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሽልማቱን ለአራት ተከታታይ ዓመታት በማሸነፍ ምርጥ የአፍሪካ አየር መንገድ መሆኑን አስመስክሯል ብለዋል። ሽልማቱም ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞችና ለስኬታማነቱ አስተዋፅኦ ላደረጉ አመራርና ሠራተኞች ከፍተኛ እውቅና ስለመሆኑም ተናግረዋል።