ለነጋዴዎች ሲሰጥ የኖረው የታክስ ነጻ እድል ለግለሰቦች ኪስ ማድለቢያ ሲውል እንደነበር የገቢዎች ሚኒስትር ይፋ አደረገ
ለነጋዴዎች ሲሰጥ የኖረው የታክስ ነጻ እድል ለግለሰቦች ኪስ ማድለቢያ ሲውል እንደነበር የገቢዎች ሚኒስትር ይፋ አደረገ
አርትስ 26/03/2011
የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ከታክስ የሰበሰበችው ገቢ እና ለነጋዴዎች የሰጠችው ከቀረጥ ነጻ ዕድል እኩል መጠን ነበረው።
እንደሚኒስትሯ ገለጻ በ2007 ዓ.ም ጀምሮ 400 ቢሊዮን ብር የታክስ እፎይታና የታክስ ነፃ እድል የተሰጠ ሲሆን ሃገሪቱ ከዘርፉ የሰበሰበችው ገንዘብ መጠንም ከዚሁ ጋር እኩል ነው።
ይህ አሃዝ ጤነኛ አለመሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ የህዝብ እና የሃገር ሃብት አላግባብ ጥቅም ላይ መዋሉን ያሳያል ነው ያሉት።
የተሰጠው የታክስ ነጻ እና እፎይታ ላልተገባ አላማ በመዋሉ የግለሰቦችን ኪስ ማድለቢያ ሆኖ ኖሯል ብለዋል። በዚህም ሃገርም ሆነ ህዝብ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም አጥተዋል ብለዋል ሚኒስትሯ።
ለዚህ ማሳያ አድርገው ካቀረቧቸው ምሳሌዎች ውስጥም በአፋር ክልል አንዲት ከተማ ስም ተሰራ የተባለው ደባ ይገኝበታል።
ሃባላ በምትባለውና የነዋሪዎቿም ቁጥር ከሁለት ሺህ በማይበልጥባት በዚህችው ከተማ 55 ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ሆቴሎች ለመገንባት በሚል ሰበብ የታክስ ነፃ ጥያቄዎች ቀርበው ፍቃድ አግኝተዋል። ነገር ግን የተባሉት ሆቴሎች አልተገነቡም።
ሸኖ ከተማ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ለመገንባት በሚል ከቀረጥ ነጻ የገባ እና ለተባለው አላማ ያልዋለ የግንባታ ግብዓት ላይም እርምጃ መወሰዱን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
ወይዘሮ አዳነች እንዳሉት በዚህ መንገድ በርካታ ብረት፣ የቤትና የቢሮ ዕቃዎችና ሌሎችም ቁሳቁሶች ያለቀረጥ እየገቡ በሃገር ውስጥ ገበያ ሲቸበቸቡ ቆይተዋል፡፡
በዚህና በተዛማጅ ምክንያቶችም ኢትዮጵያ ከታክስ የምትሰበስበው ገቢ ከብዙ የአፍሪካ ሃገራት አናሳ ደረጃ ላይ እንዲገኝ ምክንያት ሆኗል ብለዋል ።
እንደሚኒስትሯ ገለጻ በተመሳሳይም በሃገሪቱ ከባድ ችግር የሆነውን የኮንትሮባንድ ንግድ ለመከላከል በቅርቡ የጉምሩክ ፖሊስ ተቋቁሞ ወደስራ ይገባል።