ህንድ በ39 ቀናት 100 ሺህ ዜጎቿን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ አጣች፡፡
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 25፣ 2013 በህንድ የኮቪድ-19 ሟቾች ቁጥር ከ400 ሺህ በላይ ሲያሻቅብ ከዚህም ግማሽ ያህሉ ሞት በሁለተኛው ዙር ወረርሽኝ የተከሰተ ነው ተባለ፡፡ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ የተመታችው ህንድ እስካሁን ከ30 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿ በቫይረሱ መጠቃታቸውን ይፋ አድርጋለች፡፡ በህንድ 400 ሺህ 312 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ህይዎታቸውን ሲያጡ ከነዚህ መካከል 100 ሺህ የሚሆኑት የሞቱት በ39 ቀናት ውስጥ መሆኑን አልዘጂራ በዘገባው አስነብቧል፡፡
የሟቾቹ ቁጥር ከ400 ሺህ ሲሻገር በ24 ሰዓታት ውስጥ የተመዘገበው የሞት መጠን 853 መሆኑን የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ይፋ አድረጓል፡፡ አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች ግን ህንድ የታማሚዎችንም ሆነ የሟቾችን ቁጥር በትክክል ሪፖርት ብታደርግ ኖሮ ውጤቱ ከዚህ በእጅጉ የተለየ ይሆን እንደነበር ነው የሚናገሩት፡፡
ባለሞያዎቹ ቫይረሱ በከፋ ደረጃ ያጠቃት ህንድ አነሰ ቢባል 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎቿን በኮቪድ-19 ሳታጣ አትቀርም ባዮች ናቸው፡፡ ለዚህ ጥርጣሬያቸው መነሻ የሚሆነው ደግሞ ቢሃር የተባለችው የህንድ ግዛት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሪፖርቷን እንድታስተካክል ሲደረግ ቀደም ሲል ያስተላለፈችው 5 ሺህ 424 የኮቪድ ሞት ወደ 9 ሺህ 429 ከፍ ብሎ መገኘቱ ነው፡፡