ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኢትዮጵያን አንድነት አደጋ ውስጥ የሚከትቱ ሃይሎችን አንታገስም አሉ
ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላትም በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡
ተሳታፊዎቹ ከውጭ ሀገራት ጥሪ ተደርጓላቸው ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የተመለከቱ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽም በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱን ጠቅሰው የፖለቲካ ፓርቲዎች በውድድሩ አሸናፊ ሆኖ ለመገኘት ህዝብን አንድ አድርጎ ሀገሪቱን ወደ ኢኮኖሚ እድገት ለመምራት የሚያስችል ጠንካራ ሃሳብ ሊኖራቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡
ማንም ግለሰብ በንግግር እና በጽሁፍ መንግስትን መተቸት ይችላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ነገር ግን የኢትዮጵያን አንድነት የሚገዳደር ማንኛውንም አካል በምንም መልኩ አንታገስም ነው ያሉት ፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች በቂ ጊዜ ስለሌላቸው በፍጥነት መደራጀት እና መጠንከር አለባቸው ያሉ ሲሆን ዴሞክራሲያዊነትን በራሳቸው ፓርቲ ውስጥ መለማመድና ማጎልበት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊትን በተመለከተ ከምክር ቤቱ ለተነሳላቸው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ህገ መንግስቱ ለመከላከያ ሰራዊት የሰጠው ተግባር የሀገር ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ እና በክልሎች ከአቅም በላይ የሆነ አለመረጋጋት ሲከሰት በሚደረግለት ጥሪ መሰረት ገብቶ ማረጋጋት ነው ይህንን ሃላፊነቱንም ሲወጣ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡
በአንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በየጊዜው የሚነሱ ግጭቶች እና መንስኤዎቻቸውን በተመለከተ ዶክተር አብይ ለምክር ቤቱ በሰጡት ማብራሪያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ለፖለቲካ አጀንዳቸው ማስፈጸሚያነት የሚጠቀሙ እና የተማሪዎችን ህይወት በከንቱ እንዲቀጠፍ ሌት ተቀን የሚሮጡ የፖለቲካ ሃይሎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር በአዲስ መልክ መደራጀትን በተመለከተ ሲናገሩም ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውስጥ ኮንትሮባንድ ከህጋዊው አሰራር እኩል ሲሰራበት መቆቱን ገልጸው ሚኒስትሩ በአዲስ መልክ የተደራጀው ይህንን ችግር ለመፍታት ነው ብለዋል፡፡
በሀገር ውስጥ ከተከሰተው የዜጎች መፈናቀል ጋር ተያይዞ ከምክር ቤቱ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ሰዎችን በሀገራቸው ማፈናቀል ኢ ህገመንግስታዊ እና ኢ ሰብዓዊ አስጸያፊ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
መንግስት ግጭቶችን ለማምከን እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
የክልል እንሁን ጥያቄ በመንግስት በኩል እንዴት ይታያል የሚል ጥያቄ ከምክር ቤቱ ተነስቷል፡፡ የክልል ጥያቄዎች ህገ መንግስታዊ ናቸው ያሉት ዶክተር አብይ፤ጥያቄዎቹንም በህግ አግባብ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ሌላው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በማብራሪያቸው ያነሱት ጉዳይ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ነበር። ይህንን ግድብ መጨረስ ለኢትዮጵያ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድቡን በአራት አመት ለማጠናቀቅ መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡
ሚዲያዎች መጫወት ያለባቸውን ሚና እየተጫወቱ አለመሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት በስሩ ያሉትን ሚዲያዎች ለማስተካከል እየሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለእነዚህና ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው በርካታ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡