የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2010 በጀት ዓመት ካቀድኩት ማሳካት የቻልኩት 49.5 በመቶ ብቻ ነዉ አለ፡፡
አገልግሎቱ ለ468 ሺህ ደንበኞች ኤሌክትሪክ ለማዳረስ አቅዶ ለ231 ሺህ 781 ደንበኞች ብቻ ነው ኤሌክትሪክ ማድረስ የቻልኩት ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የ2010 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም እና የ2011 በጀት አመት ዕቅድን ዛሬ ባቀረበበት ወቅት የተቋሙ ምክትል ስራ አስፈጻሚና የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ብዙወርቅ ደምሰዉ ኃይል በማምረት ደረጃ ሰፊ ስራዎችን ማከናወን ቢችልም ለተጠቃሚዎች በማዳረስ ረገድ አሁንም ክፍተቶች አሉብን ብለዋል፡፡
ለዚህም የፋይናስ አለመኖር፣ የግብዓት አቅርቦት እጥረት፣ ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖር እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አለመደገፉ ለችግሩ እንደምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡
የፋይናንስ አቅምን ማሳደግ ፣የአቅርቦት ችግሮችን መፍታት፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መተግበር እና የአዳዲስ ተጠቃሚዎችን ቁጥር መጨመር ተቋሙ በ2011 በጀት ዓመት በዋናነት የሚሰራባቸዉ ጉዳዮች እንደሆኑ አገልግሎቱ ተናግሯል፡፡