የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን መቋቋም ለዓመታት ሲንከባለሉ ለመጡ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ያግዛል ተባለ
የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን መቋቋም ለዓመታት ሲንከባለሉ ለመጡ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ያግዛል ተባለ
አርትስ 15/04/2011
በጉዳዩ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የተሰጠዉ መግለጫ እንዳስታወቀዉ ፤ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን፤ የህዝብን ጥያቄን ለመፍታት በጥናት ላይ የተመሠረተ የውሳኔ ሐሳብ ለማቅረብ ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡
ለህዝቦች ጥቅም፤ መብት እና ነጻነት በጋራ እና በተደጋጋፊነት ለማሳደግና አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሥራዎችን መንግሥት እያካሄደ ነው፡፡
በመግለጫዉም ከሰፊ የሪፎርም ሥራ ጎን ለጎን የሀገራችንን ዘለቄታዊ ሰላምና የሕዝቦችን ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ እንዲቻል ፤በተለያዩ ጊዜያት እየተነሡ ያሉ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮችን በሳይንሳዊ ዘዴ በማጥናት የመፍትሔ ሐሳብ የሚያቀርብ ኮሚሽን በአዋጅ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡
ኮሚሽኑ በዚህ ጊዜ የተቋቋመው ከማንነት ፣ ከአስተዳደር ወሰን እና ከራስ በራስ አስተዳደር ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ በሃገሪቱ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ስፋትና እያስከተሉ ያሉት ጥፋቶችን ለመከላከል እንዲቻል ተደርጎ ነዉ ፡፡
በአሁኑ ወቅት ከሁሉም ማዕዘናት ማንነትንና የአስተዳደር ወሰንን በተመለከተ እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች በመደበኛ ሥርዓቱ ለመፍታት ሕገ መንግስታዊ አካሄድ እንዳለ ግልጽ ነው፤ሆኖም እነዚህ ጉዳዮች እና
ተመሳሳይ የመብት ጉዳዮች ጥያቄ ሲቀርብ ወይም አለመግባባት ሲኖር በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 48 እና አንቀፅ 62 ንኡስ አንቀፅ 3 እና 6 መሰረት ዉሳኔ የመስጠት ስልጣን የፌደሬሽን ምክርቤት እንደተሰጠዉ ይታወቃል ብሏል መግለጫዉ፡፡
በማንነትንና የአስተዳደር ወሰንን በተመለከተ እየተነሱ ላሉ ጥያቄዎች “በሕገ መንግሥቱ ምላሽ አግኝተዋል” በሚል ጥቅልና የግብር ይውጣ አያያዝ ጋር በተገናኘ አግባብ የሆኑት ጥያቄዎች በሕገ መንግሥቱ እና በአዋጁ በተገለጸበት አኳኃን ለሚመለከተው ክልል እና ፌደሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ የማይቀርብበት ሁኔታ በመኖሩ የአገሪቱን ሕልውና አደጋ ላይ በመጣል ላይ ይገኛል፡፡
ጥያቄዎቹ ከብዛታቸው እና ከግጭት ባሕሪውያቸው ምክንያት በሕዝቦች ሰላምና ደህንነት ላይ እየጋረጠ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ እናም ኮሚሽኑ ተጨባጭ አደጋና ስጋት እየፈጠሩ ያሉ እነዚህ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባብሰው ለአገር ህልውና ሥጋት የማይሆንበት ሁኔታ ለመፍጠር በመስኩ ምሁራን ጥልቀት ያለው ጥናት በማድረግ ሳይንሳዊ የሆነ ምክረ ሃሳብ ለሚመለከተው የመንግስት አካላት የማቅረብ ዓላማ አለዉ ተብሏል፡፡