ዚነዲን ዚዳን በድጋሜ የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ሁኖ ተሽሟል፡፡
ዚነዲን ዚዳን በድጋሜ የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ሁኖ ተሽሟል፡፡
ፈረንሳያዊው የ46 ዓመት አሰልጣኝ ዚነዲን ያዚድ ዚዳን አርጀንቲናዊውን አሰልጣኝ ሳንቲጎ ሶላሪ በመተካት የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ በመሆን ተቀጥሯል፡፡
ዚዳን ከአስር ወራት በፊት የሎስ ብላንኮሶች አሰልጣኝ የነበረ ሲሆን በቆይታው ለሶስት ተከታታይ ዓመታት የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን፤ የላ ሊጋን እና ሌሎች ተጨማሪ አምስት ዋንጫዎችን ክልቡ እንዲያሳካ ካደረገ በኋላ በወርሀ ግንቦት 2018 ነበር ከሳንቲያጎ ቤርናባው ኃላፊነት የተነሳው፤ አሁን ደግሞ ለአምስት ወራት ያህል ክለቡን ሲመራ ከነበረው ሶላሪ በመረከብ እስከ 2022 ድረስ ቡድኑን ለማሰልጠን በይፋ ተረክቧል፡፡
ዚዳንም በድጋሚ ወደ ቤቱ በመመለሱ መደሰቱን አስታውቋል፡፡ ክለቡ አሁን በላ ሊጋው ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ከሊጉ መሪ ባርሴሎና በ12 ነጥብ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
ፈረንሳያዊው አሰልጣኝ ከኃላፊነቱ እንደተነሳ ሰፔናዊው አሰልጣኝ ዩሊዬን ሎፔቴጉይ ቡድኑን መረከብ ቢችሉም ውጤታማ ባለመሆናቸው፤ ከአራት ወራት ከግማሽ በኋላ በተጠባባቂ ቡድኑ አሰልጣኝ ሳንቲያጎ ሶላሪ ተረክቦ ህዳር ወር ላይ እስከ 2021 ድረስ የሚያቆየውን ቋሚ ውል ተሰጥቶት ነበር፤ ነገር ግን ባለፈው ሳምንት ክለቡ ከሶስት ውድድሮች ውጭ የመሆን ደረጃ ላይ መድረሱ የክለቡ ውጤታማነት መውረድ ለስንብቱ ዋንኛ ምክንያት ነው፡፡
ማድሪድ ከአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ እና ኮፓ ዴል ሬይ ውድድሮች የተሰናበተ ሲሆን በላ ሊጋው ተስፋ ያለው አይመስልም፤ በዚህም ዓመቱን ያለዋንጫ የሚያጠናቅቅ ይመስላል፡፡
ዚነዲን ዚዳንም በአዲሱ ኃላፊነት ቡድኑን በድጋሜ የመገንባት፤ የክርስቲያኖ ሮናልዶ ተተኪ ተጫዋች ማስፈረም እና ሎስ ብላንኮሶቹን ወደ ክብራቸው እና የድል ጎዳና መመለስ ይጠበቅበታል፡፡ ከወዲሁም ቤልጅየማዊው ኤዲን ሃዛርድ እና ሌሎች ኮከቦች ስማቸው ከክለቡ ጋር በሰፊው እየተነሳ ይገኛል፡፡
ዚዳን በማድሪድ ቤት በተጫዋችነት ከ2001 – 2006 ድረስ ሲያገለግል በአሰልጣኝነት ደግሞ ከ2016 – 2018 ድረስ አሰልጥኗል፡፡