ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወሙበት ሰልፍ በኒውጄርሲ ሊካሄድ ነው፡፡
አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2014 ሰላማዊ ሰልፉ መጋቢት 1 ቀን 2014 ዓ.ም በአሜሪካ ኒውጄርሲ ግዛት እንደሚካሄድ የኒውዮርክ ኒውጄርሲ ተስፋ ለኢትዮጵያ ድርጅት ዋና ሰብሳቢ አቶ አክሊሉ ታፈሰ ለኢዜአ ገልጸዋል። ሕጉን ያረቀቁት የኒውጄርሲ የኮንግረስ አባል ቲም ማሊኖውስኪ በሚሰሩበት ቢሮ ፊት ለፊት እንደሚከናወንና እሳቸውንና ሕጉን የሚቃወሙ መልዕክቶች በሰልፉ ላይ እንደሚተላለፉ አመልክተዋል።
ሕጉን በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት እንደሚቃወሙትና የኮንግረስ አባሉ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የሚያሳስብ ደብዳቤ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል። “ቶም ማሊኖውስኪ ያረቀቁት ሕግ ለረጅም ጊዜ የቆየውን የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት የሚጎዳና የማይጠቅም ነው፤ ማሊኖውስኪ እየፈጸሙት ያለው መልካም ያልሆነ ተግባር በሚኖሩበት ግዛት የመረጧቸው ዜጎች እንዲያውቁት እናደርጋለን” ብለዋል አቶ አክሊሉ።
ረቂቅ ሕጉ ኤርትራንም የሚመለከት በመሆኑ በሰልፉ ላይ በአሜሪካ የሚገኙ ኤርትራውያንም እንደሚሳተፉበት ጠቁመዋል። በቀጣይ በአሜሪካ ትላልቅ ከተሞች ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወሙ ሰላማዊ ሰልፎችን ለማካሄድ መታሰቡንም አመልክተዋል። ረቂቅ ሕጉ በአሜሪካ ኮንግረስ ለውይይት ቀርቦ ውሳኔ እንዳይሰጥበት ለማድረግ የተቃውሞ ዘመቻዎች እየተካሄዱ እንደሚገኙ ነው አቶ አክሊሉ የገለጹት።
በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ-ኢትዮጵያውያን የመረጧቸውን በየአካባቢያቸው የሚገኙ የኮንግረስ አባላት በማነጋገር፣ ደብዳቤ በመጻፍና በማህበራዊ ትስስር ገጾች ዘመቻ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ ብለዋል። ረቂቅ ሕጉ ኢትዮጵያን በዘር ማጥፋት የመክሰስ ዓላማ ያለው ሲሆን ቪዛና ጉዞን ጨምሮ በአጠቃላይ በኢሚግሬሽን ጉዳዮች ላይ ገደብ ሊጥል እንደሚችል ያስቀምጣል።