አሜሪካና ኢራን የየመንን የሰላም ድርድር አደነቁ
አሜሪካና ኢራን የየመንን የሰላም ድርድር አደነቁ
አርትስ 05/04/2011
ከበርካታ ዓመታት ወዲህ ዋሽንግተንና ቴህራን አንድ ቋንቋ የተናገሩበት ጉዳይ ቢኖር የየመን ተዋጊ ሀይሎች በሁዴይዳ ወደብ ተኩስ ለማቆም ያደረጉት ስምምነት ነው፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አደራዳሪነት በየመን መንግስትና በሁቲወች መካከል የተደረገውን የሰላም ድርድር እና ውጤት ሁለቱም ሀገራት በመልካም ጎኑ እንደሚያዩት ገልፀዋል፡፡
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ ሁለቱ ወገኖች የደረሱበትን ስምምነት የሚያበረታታ በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ባህራም ጋሲሚ በበኩላቸው ድርድሩን ተስፋ ሰጭ እርምጃ ካሉ በኋላ ሳይውል ሳይድር ቀጣዩን ውይይት አድርገው የመጨረሻ ውጤት ላይ መድረስ አለባቸው ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ብዙወች ከባድ አድርገው የሚመለከቱትን ነገር እኛ ሞክረነዋል፤ ቀጣዩ ስራችን ቀላል ባይሆንም የማይቻል ነገር ስለሌለ ጥሩ ውጤት እንጠብቃለን ብሏል፡፡
ፖምፒዮ የዚህ ድርድር የመጨረሻ ውጤት በየመን የአዲስ ህይወት ምእራፍ መጀመሪያ ይሆናል፤ ከልብ ከተሰራ ደግሞ ሰላምን ማምጣት ይቻላል ብለዋል፡፡
በነገሩ እጇ በትልቁ አለበት ተብላ የምትተቸው ሳውዲ አረቢያም ብትሆን የተኩስ አቁም ስምምነቱን ይበል የሚያሰኝ ብለዋች፡፡
የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሁዴይዳ ወደብ ከተዋጊ ሀይሎች ይዞታ ነፃ መሆን የእርዳታ ቁሳቁሶችን በወቅቱ ለማድረስ ስለሚረዳ ለሚሊኖች ትልቅ ተስፋ ነው ብለዋል፡፡