በግመል የኮንትሮባንድ ንግድ ሲካሄድ ተያዘ።
ግምታዊ ዋጋቸው 937ሺህ 912 የሆኑ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ለኮንትሮባንድ ክትትል ቡድን በደረሰ ጥቆማ መሠረት በዚህ ሳምንት መያዛቸውን በገቢዎች ሚኒስቴር የጉምሩክ ኮሚሽን የድሬዳዋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ገለጸ፡፡
አዳዲስና ልባሽ ጨርቆች እንዲሁም ሲጋራዎች በግመል ተጓጉዘው ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጀርባ በተለምዶ መርመርሳ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በተራገፈበት በጉምሩክ ሠራተኞች፣ በፌደራል እና በድሬዳዋ አድማ ብተና ፖሊሶች አማካኝነት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የቅ/ጽ/ቤቱ የሕግ ተገዥነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ በፍቃዱ ገመችስ ገልጸዋል፡፡
አቶ በፍቃዱ እንደገለጹት፤ የኮንትሮባንድ እና ሌሎች የጉምሩክ ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ መረጃ ወሳኝ በመሆኑና ለዚህም አስተዋጽኦ ለሚያደርጉ ጠቋሚዎች፣ ያዦች፣ ተባባሪዎችና ደጋፊዎች ካደረጉት ተሳትፎ ጋር የተመጣጠነ ወሮታ ይከፈላቸዋል፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ የጉምሩክ ክልል በየትኛውም ስፍራ ሕገ-ወጥ ዕቃ መኖሩን የሚያውቅ ማንኛውም ሰው ወዲያውኑ በአቅራቢያው ለሚገኝ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ወይም ህግ አስከባሪ አካል ማሳወቅ አለበት፡፡
ይህ በሚደርግበት ጊዜ ጥቆማ ከማይቀርብባቸው ሁኔታዎች በስተቀር ለሚኒስቴር መ/ቤቱ በሚቀርብ ጥቆማ ከተያዘ የሕገ-ወጥ ዕቃዎች መረጃ አሰጣጥ፣ አያያዝ፣ አመዘጋገብ እና የወሮታ ክፍያዎችን መመሪያ ቁጥር 78/2004 መሠረት የወሮታ ክፍያ ስለሚከፈል ማህበረሰቡ ሕገ-ወጦችን ከመከላከል በተጨማሪ በመጠቆም ተጠቃሚ እንዲሆን ም/ሥራ አስኪያጁ ጥሪያቸው አቅርበዋል።ምንጭ ገቢዎች ሚኒስቴር