በሪል ስቴት ኩባንያዎች ላይ የተጣለው ዕግድ እንዲነሳ መመርያ ተሰጠ
በሪል ስቴት ኩባንያዎች ላይ የተጣለው ዕግድ እንዲነሳ መመርያ ተሰጠ
የመሬት ቢሮ ያቆመውን አገልግሎት በድጋሚ መስጠት ጀመሯል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ለሪል ስቴት ኩባንያዎች መስጠት አቁሞ የነበረውን አገልግሎት በድጋሚ መስጠት እንዲጀምር መመርያ ሰጡ፡፡
ፍርድ ቤት እንጂ የፌዴራል ፖሊስ የማገድ ሥልጣን ስለሌለው፣ የሪል ስቴት ኩባንያዎች ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡
በሪል ስቴት ልማት ዘርፍ የተከሰተውን ችግር ለመፍታት ምክትል ከንቲባው ከሪል ስቴት ኩባንያዎች ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
በዉይታቸዉም ከአንድ ወር በፊት የፌዴራል ፖሊስ፣ በወንጀል የጠራጠራቸውን 28 የሪል ስቴት ኩባንያዎች እንዲታገዱ ለክፍለ ከተሞች ደብዳቤ በመጻፉ የተፈጠረው ችግር ነው፡፡ ከተዘረዘሩት 28 ሪል ስቴት ኩባንያዎች መካከል፣ በሪል ስቴት ልማት ምንም ተሳትፎ እንደሌላቸው የገለጹና በዝርዝሩ ውስጥ በመካተታቸው ብቻ ሌሎች ሥራዎቻቸው ላይ ተፅዕኖ በመፍጠሩ እንዲስተካከል የጠየቁም አሉ፡፡
ምክትል ከንቲባው በሰጡት መመርያ በሪል ስቴት ልማት ዘርፍ በአስተዳደሩና በግል ተዋናዮች በኩል ያሉ ችግሮችን ለይቶ፣ በግንባታ ቦታ ላይ ተገኝቶ ችግሩን የመፍታት ሥልጣን የተሰጠው ግብረ ኃይል ተቋቁሟል፡፡
ግብረ ኃይሉ በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የሚመራ ነው፡፡ ከፕላን ኮሚሽን፣ ከኮንስትራክሽን ቢሮ፣ ከገቢዎች ቢሮ፣ ከግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣንና ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት የተውጣጡ አባላት ይኖሩታል፡፡
ሪፖርተር እንደዘገበዉ ከዚህ በተጨማሪ ከሪል ስቴት ኩባንያዎች በተለይም ፀሐይ ሪል ስቴትና ሰንሻይን ሪል ስቴት የተካተቱ ሲሆን፣ ግብረ ኃይሉ የሚያካሂደውን ሥራ ምክትል ከንቲባው በቀጥታ እንደሚከታተሉ ታውቋል፡፡